ፕሬዚዳንቱ ወደ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ሳውዲ አረቢያ በመጓዝ በመካከለኛው ምስራቅ ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ቀጠሮ ይዘዋል ተብሏል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ እንዳሉት፤ የሩሲያው መሪ በጉብኝታቸው በሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በነዳጅ ዘርፍ ትብብር፣ በዓለም አቀፍ እና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሁም እየተካሄደ ስላለው የእስራኤል እና የፍልስጤም ግጭት ክሁለቱ ሀገራት መሪዎች ጋር ይወያያሉ።
ቃል አቀባዩ እክለውም በመጪው ሐሙስ ፑቲን ከኢራኑ አቻቸው ኢብራሂም ራይሲ ጋር በሞስኮ እንደሚገናኙ አስታውቀዋል። የኢራን የዜና ወኪል ራይሲ ከከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንዲሁም ከሀገሪቱ የንግድ እና ኢኮኖሚ ልዑካን ቡድኖች ጋር ወደ ሩሲያ እንደሚያቀኑ ዘግቦ ነበር።
ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች በሞስኮ እና ቴህራን መካከል ስላለው የንግድ፣ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካዊ ትብብር እንዲሁም በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የፑቲን የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝት የሚደረገው የዓለማችን ግዙፍ የነዳጅ ዘይት አምራች ሀገራትን ያቀፈው እና በሳዑዲ አረቢያ እና በሩሲያ የሚመራው ኦፔክ+ በቀን ወደ 2.2 ሚሊዮን በርሜል የሚጠጋ የምርት ቅነሳን እንደሚያደርግ ባለፈው ሳምንት ይፋ ካደረገ በኋላ መሆኑን አርቲ ዘግቧል።