"የባህል ህክምና እንሰጣለን የሚሉ አጭበርባሪ ግለሰቦች እየተበራከቱ ነው"፡- የአዲስ አበባ ባህል መድኃኒት አዋቂዎች ማህበር

2 Mons Ago
"የባህል ህክምና እንሰጣለን የሚሉ አጭበርባሪ ግለሰቦች እየተበራከቱ ነው"፡- የአዲስ አበባ ባህል መድኃኒት አዋቂዎች ማህበር
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ ፌስ ቡክ እና ቴሌግራም ያሉ ማኅበራዊ መገናኛዎችን በመጠቀም "የባህል መድሃኒት አዋቂዎች ነን" የሚሉ እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
 
እነዚህ መድሃኒት አዋቂ ነን የሚሉ ሰዎች መድሃኒት እናዘጋጅላቸዋለን የሚሏቸው ጉዳዮች ያልተለመዱና ‹‹መድሃኒት›› ይፈታቸዋል የማይባሉ ዓይነት ናቸው፡፡
 
ለምሳሌ ለገበያ፣ ለስልጣን፣ ለግርማ ሞገስ፣ ትዳር እምቢ ላለው፣ ወደ ውጭ ለሚጓዝ፣ ሎተሪ እንዲደርሳችሁ ወዘተ… የሚሉ አጓጊ ቃላትን ይጠቀማሉ፡፡
 
መድሃኒት አዋቂ ነን ከሚሉት ሰዎች ‹‹መርጌታ›› የሚል መንፈሳዊ ማዕረግን የሚጠቀሙት ብዙዎቹ ሲሆኑ፤ በመቶ ሺዎች ተከታዮች ባሏቸው የማኅበራዊ መገናኛዎች ላይ ስልክ ቁጥሮቻቸውን ከመለጠፍ ባለፈ የሥራ አድራሻቸውን በግልጽ አያስቀምጡም፡፡
 
ስልክ ሲደወልላቸው ‹‹ምን መድሃኒት ትፈልጋለህ?›› ብለው ይጠይቁና ለማንኛውም ዓይነት ችግር መፍትሔ እንዳላቸው ይናገራሉ፤ ባለጉዳዩ ክፍያ በባንክ እንዲያስገባ መድሃኒቱንም በመልዕክተኛ እንደሚልኩ ይናገራሉ፡፡
 
በዚህ መልኩ በርካታ ማጭበርበሮች እንደደረሰባቸው የገለጹት የእውነትን ፍለጋ ራድዮ ፕሮግራም አድማጮች ሲሆኑ፤ የፕሮግራሙ አዘጋጅ ጉዳዩን ለማጣረት ባደረገው የስልክ ሙከራ ነገሩ የማጭበርበር መሆኑን ለመለየት ችሏል፡፡
 
ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የአዲስ አበባ የባህል መድሃኒት አዋቂዎች ማህበር ፕሬዚደንት መሪጌታ መንግሥቱ ከእውነትን ፍለጋ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዲህ ያለ ሥራ የሚሠሩ አጭበርባሪዎች መበራከታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በራሴ ሥም መሪጌታ መንግስቱ የባህል መድሃኒት አዋቂ›› የሚል ገጽ ተከፍቶ ሰዎች እየተጭበረበሩ ነውም ብለዋል፡፡
 
ከመንግስት ጋር እየተነጋገርን እነዚህን አጭበርባሪዎች ለማስታገስ እየሞከርን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
 
የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 እውነትን ፍለጋ ራድዮ ፕሮግራም ባደረገው ማጣራት፤ እነዚህ መድሃኒት አዋቂ ነን ብለው የሚያስተዋውቁ ሰዎች፤ እንፈውሳቸዋለን የሚሏቸው በግልጽ መድሃኒት እንደሌላቸው የተነገረላቸው በሽታዎች፤ ለምሳሌ ኤች አይ ቪ. አስም፣ ደም ብዛት፣ ካንሰር፣ ስኳር ወዘተ… ናቸው፡፡
 
በተጨማሪም በሽታ ሊታዩ የማይችሉ ወይም በሽታ ስለመሆናቸው ያልተረጋገጡ ለሆኑ ነገሮች ህክምና እንሰጣለንም ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ራዕይ ለማየት፣ ሌሊት ሽንቱ ለሚያመልጠው፣ ለወር አበባ፣ ለንቃተ ህሊና፣ ትምህርት ለማይገባው፣ ለሥራ ዕድል፣ ለመስተፋቅር ወዘተ… የሚሉ አሉ፡፡
 
ህክምና ፈላጊዎች እንዲህ መሰል በሆኑ አጭበርባሪዎች እንዳይታለሉ ሲሉ የአዲስ አበባ የባህል መድሃኒት አዋቂዎች ማህበር ፕሬዚደንት መሪጌታ መንግሥቱ ተናግረዋል::
 
ደሳለኝ ስዩም አዘጋጅቶታል

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top