በ2007 ዓ.ም በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የተነሳውን እሳት ለማጥፋት ጥረት ሲያደርግ ህይወቱ ያለፈው ቢኒያም አድማሱ የሕይወት ዘመን እውቅና ተሰጠው።
ለአካባቢ ጥበቃ ጀግናው - ቢኒያም አድማሱ እውቅናው የተሰጠው ፓርኩ በዩኔስኮ መመዝገቡን ምክንያት በማድረግ በባሌ ሮቤ በተካሄደ የማስተዋወቅና የእውቅና መርሃ ግብር ላይ ነው።
ከዚህ በፊት ለወጣቱ መታሰቢያ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የመታሰቢያ ሀውልት ቆሞለት እንደነበርም ይታወሳል።
ወጣቱ መጋቢት 2007 ዓ.ም በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ የተነሳውን እሳት ለማጥፋት የስራ ባልደረቦቹን እና የአካባቢውን ሰዎች በማስተባበር ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ ንፋስ የእሳቱን አቅጣጫ በድንገት ወደ ወጣት ቢኒያም በመቀየሩ ምክንያት ህይወቱ እንዳለፈ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡
ወጣት ቢኒያም አድማሱ በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ላይ በሚሰራው ፍራንክ ፈርት ዞሎጂካል ሶሳይቲ (Frankfurt Zoological Society) በሚባል ዓለም አቀፍ የግብረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ የቱሪዝምና አካባቢ ጥበቃ ባለሙያ በመሆን ለፓርኩ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጉ ተጠቅሷል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ ፓርኩ በቋሚ ቅርስነት እንዲመዘገብ ጉልህ አበርክቶ ለነበራቸው ባለድርሻ አካላትና ግለሰቦችም ዕውቅና ተሰጥቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ በዩኔስኮ ቋሚ ቅርስነት በማስመዝገብ ረገድ ብዙ መስዋዕትነት መከፈሉን አመልክተዋል።
በተለይም እስከ ህይወት መስዋዕትነት ድረስ የከፈሉ እንደ ቢኒያም አድማሱ ያሉ ወጣቶች ሁሌም በታሪክ እንደሚታወሱ ተናግረዋል።
በአገሪቱ የሚገኙ ብርቅዬ የተፈጥሮ ሀብቶችን በመጠበቅ ለቱሪዝም መዳረሻዎች በማድረግና የሀገሪቱ የሀብት መፍጠሪያ አማራጭ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሯ አንስተዋል።
ሽልማቱን የተቀበሉት የቢንያም ወላጅ አባት አቶ አድማሱ ቀጭኑ በበኩላቸው "ልጄ የህይወት መስዋዕትነት የከፈለለት ብሔራዊ ፓርክ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱ አስደስቶኛል'' ብለዋል።
ሁሉም የአካባቢው ነዋሪ የተፈጥሮ ኃብትን በመንከባከብ በኩል የድርሻውን እንዲወጣም መጠየቃቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው።
ፓርኩ ዋቤ ሸበሌ፣ ዱማል፣ ያዶትና ወልመል የተሰኙ ወንዞች የሚፈሱበትና ቀይ ቀበሮ፣ የደጋ አጋዘንና ሌሎችም ብርቅዬ የዱር እንስሳት፣ አዕወፋትና ዕጽዋት መገኛ መሆኑ ይታወቃል።