በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ እንሰራለን፡ - ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

2 Mons Ago
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ እንሰራለን፡ - ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በመፍታት የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ህዝብን ባሳተፈ መልኩ እንሰራለን ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወላይታ ሶዶ ማዕከል ከሚገኙ የክልል ቢሮ አመራር አባላትና ሰራተኞች ጋር በቀጣይ የስራ ሂደትና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ተወያይተዋል።

በመንግሥት ተቋማት የሚስተዋሉ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች፣ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መመለስ በሚያስችሉ የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ ነው የተናገሩት።

ለዚህም የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ግልጽና ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት እንዲያቀርቡ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ ሰራተኛውም የህዝብን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ አገልግሎት በመስጠት የሚጠበቅበትን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ክልሉ የተቸረው በርካታ የተፈጥሮ ፀጋና ከፍተኛ የመልማት አቅም እንዲሁም የህዝቡ የስራ ተነሳሽነት መኖሩን ጠቁመው፤ እነዚህም ክልሉን ለመለወጥና የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ የሚያስችሉ መልካም አጋጣሚዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ስለሆነም አዳጊ ፍላጎቶች የሚወልዷቸውን ጥያቄዎች ጨምሮ አገልግሎቶችን በማዘመንና በወቅቱ በመመለስ ተምሳሌት የሚሆን ክልል ለመፍጠር መትጋት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

የህዝብን የአደረጃጀት ጥያቄ ዘላቂ ልማትና አብሮነትን በሚያረጋግጥ መልኩ መመለስ መቻሉን አመልክተው፤ አሁን "እቅዶቻችንን ወደ መሬት በማውረድ ህዝባችንን በልማት ለመካስ ጥረቱ ሊጠናከር ይገባል" ብለዋል።

በስራ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ወቅታዊ በመሆናቸው በብቃት በመወጣትና በመቋቋም የተሻለ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚቻል አስረድተዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል አስተያየታቸውን የሰጡት የተለያዩ መስሪያ ቤት ሰራተኞችም አቅማቸው በፈቀደ ሁሉ ህዝብን በትጋት ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስ ቢሮ የሰው ሀብት ልማት ኢንስፔክሽን ባለሙያ የምስራች አለማየሁ በሰጡት አስተያየት፤ ክልሉ የሽግግር ወቅት በመሆኑ ፈታኝ ተግዳሮቶች ቢኖሩም ያንን ተቋቁሞ ለለውጥ መስራት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

"ህብረተሰቡን በተቀላጠፈ የአገልግሎት አሰጣጥ ለማገልገል ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በክልሉ የፋይናንስ ቢሮ የልማትና እቅድ ባለሙያ አቶ ዮሴፍ አደም በበኩላቸው፤ "መድረኩ ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ግልፀኝነትን በመፍጠር ለመወያየት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል" ብለዋል።

"አመቺ የስራ ቦታና መሠል ተግዳሮቶች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ እሙን ነው ፈተናዎችን በፅናት በመሻገር የብልፅግና ጉዟችንን እውን ለማድረግ እንተጋለን" ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በውይይት መድረኩ የክልሉ ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ ሃላፊን ጨምሮ በወላይታ ሶዶ ማዕከል አገልግሎት የሚሰጡ መስሪያ ቤቶች ሰራተኞች መሳተፋቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

 

 

 

 

 

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top