በዲላ ማዕከል 3ኛ እና 4ኛ ዙር የአመራር አቅም ግንባታ ሰልጣኞች 1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ በማዋጣት በአካባቢው የተለያዩ በጎ ተግባራትን አከናውነዋል።
ሰልጣኞቹ በዛሬው ዕለት ከ 600 ሺህ ብር በላይ በማሰባሰብ በዲላ ከተማ ለሚገኘው ቆፌ አንድኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ዴስክ ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ በ 3ኛ ዙር የአቅም ግንባታ ሰልጣኞች ከ 565 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ የአቅም ደካሞችን ቤት ለባለንብረቶቹ አስረክበዋል።
በወቅቱ የተገኙት የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)፤ የመንግሥት አመራር አቅም ግንባታ ሰልጣኞች እያከናወኑ የሚገኙት ተግባር ተምሳሌታዊና ሊጠናከር የሚገባው ተግባር ነው ብለዋል።
ድጋፉን ያገኙት የቆፌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እንዲሁም መምህራን ያገኙትን ድጋፍ ወደ ተግባር በመቀየር በትምህርት ዘርፉ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ካሊድ አልዋን፤ ድጋፉ ኢትዮጵያዊያን መረዳዳት እና መደጋገፍ ከቻሉ በርካታ ችግሮቻቸውን በመፍታትና ልማትን ማፋጠን እንደሚችሉ የታየበት መሆኑን ገልፀዋል።
ተማሪዎች ያሉ ችግሮችን በጥረት በመሻገር ነገ ላይ የሀገር አለኝታ እንደሚሆኑ ባለ ሙሉ ተስፋ መሆናቸውንም ሚኒስትር ዴኤታው ጠቅሰዋል።