"በሀገራችን ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው"፦ የሥነ-ልቦና ባለሙያው ዳዊት ላቀው

2 Mons Ago
"በሀገራችን ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር እያሻቀበ ነው"፦ የሥነ-ልቦና ባለሙያው ዳዊት ላቀው

በሀገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ “ራስን ማጥፋት” የሚለው ዜና እየተበራከት መጥቷል።

በተለይም አንዳንድ የማኅበራዊ ሚዲያው ተጠቃሚዎች ራሳቸውን ከማጥፋታቸው በፊት የስንብት የሚመስል መልዕክት አስፍረው ከዚያ ራሳቸውን ማጥፋታቸው ይሰማል።

ራስን ማጥፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደትልቅ የሞት መንሥኤ የሚታይ ጉዳይ መሆኑ ይገለጻል።

ኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ በዚሁ ጉዳይ ላይ ያነጋገራቸው የሥነ-ልቦና ባለሙያው ዳዊት ላቀው፣ ራስን ማጥፋት በሀገራችን እየተበራከተ መምጣቱን ይገልጻሉ።

“ራስን ለማጥፋት የተለያዩ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ” የሚሉት ባለሙያው የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነት፣ የብቸኝነት ስሜት እና ማኅበራዊ ቀውሶች ከምክንያቶቹ መካከል የሚጠቀሱ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በተለይ ወጣቱ ክፍል ላይ ራስን ማጥፋት በስፋት እንደሚስተዋል ጠቁመው፣ ብዙው ወጣት ሥራ ከማጣት፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡት ደግሞ ውጤታቸው ዝቅተኛ መሆኑ ራስን ለማጥፋት እንደ ምክንያት የሚጠቀስ መሆኑን አክለዋል።

በትምህርት እና በሕይወት ምክንያት ተስፋ በመቁረጥ የተለያዩ ሱሶች ውስጥ የሚገቡ ሰዎች መኖራቸውን እና ሱሶች በራሱ ራስን ለማጥፋት ምክንያት እንደሚሆኑም ተናግረዋል።

“ራስን ማጥፋት በሁለት መንገድ እናየዋለን” የሚሉት ባለሙያው፣ ራስን የማጥፋት ሙከራ አንዱ ሲሆን ይህም ችግር ውስጥ በገቡ እና ብስጭት በገጠማቸው ቁጥር ራሴን አጠፋለሁ በማለት የሚናገሩ ናቸው ይላሉ። 

ሁለተኛው ደግሞ አሁን ላይ እየተበራከት ያለው ወስኖ ራስን ማጥፋት ውስጥ መግባት መሆኑን ይናገራሉ። 

ራስን ለማጥፋት የትኛው የኅብረተሰብ ክፍል ተጋላጭ ነው ብለን የጠየቅናቸው ባለሙያው፣ በሀገራችን ራሳቸውን ሲያጠፉ የምንመለከታቸው በብዛት ወጣቶች ናቸው ብለዋል።

ለዚህ ጉዳይ ማኅበረሰብ እና መንግሥት የራሳቸው ኃላፊነት እንዳለባቸው እና ሰዎች ራሳቸውን ለምን ያጠፋሉ የሚል ጥናት መደረግ እንዳለበት መክረዋል።

ከትምህርት ቤት ጀምሮ ልጆች ላይ ጠንካራ ስብእና ሊገነባ እንደሚገባ እና ግንዛቤን ከመፍጠር አንሥቶ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ልጆች የሚገጥማቸውን ችግር እንዴት መፍታት እንዳለባቸው እንዲገነዘቡ መሠራት እንዳለበት ገልጸዋል።

ማኅበረሰቡ እንደዚህ ዓይነት ችግር የሚገጥማቸውን ሰዎች የሚረዳበትን ዕይታ መቀየር ያስፈልጋል የሚሉት ባለሙያው፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ የይመለከተኛል ስሜት ሊኖር እንደሚገባ ምክራቸውን ለግሰዋል።

በተስሊም ሙሐመድ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top