በ2016 በጀት ዓመት እስካሁን ከ120 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት እንዲያገኙ መደረጉን የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ገለጹ።
የውጭ ሀገር ሥራን አማራጭ ለሚያደርጉ ዜጎች መንግሥት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ሥምምነት በመፈራረም በሕጋዊ መንገድ ተሰማርተው የሚሠሩበትን ምቹ ሁኔታ እየፈጠረ ነው።
ኢትዮጵያ ከሊባኖስ፣ ጆርዳን፣ ኳታር እና የተባበሩት ዓረብ ኢምሬቶች ጋር ሕጋዊ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ውል በመዋዋል ዜጎች በሕጋዊ መንገድ ሄደው እንዲሠሩ እየተደረገ ይገኛል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል፣ የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ዜጎች ደኅንነታቸው ተጠብቆ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት ዕድል እየተፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።
የውጭ ሀገር የሥራ ሥምሪት ለሚወስዱ ዜጎች ብቻ ተብለው በተለዩ 94 የሥልጠና ማዕከላት የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የቋንቋ ችሎታቸውን የሚያጎለብቱበት፤ ገንዘባቸውን በአግባቡ ማስተዳደር የሚችሉበት፣ ስለሚሄዱባቸው ሀገራት በቂ ግንዛቤ የሚይዙበት እና የቴክኖሎጂ አቅማቸውን የሚያሳድጉበት ልዩ ሥርዓተ ሥልጠና መሆኑንም ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ የዜጎችን የውጭ ሀገር ሥራ የመሠማራት ፍላጎት በሕጋዊ መንገድ ለማሳካት ከተለዩ ሀገራት ጋር በመነጋገር እና ሥምምነት በመፈራረም መዳረሻዎችን እያሰፋች መሆኑንም ገልጸዋል።
የመዳረሻ ሀገራትን ቁጥር ለማብዛት እየሠራ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም መካከለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓ እና እስያ ሀገራት የሥራ ፍላጎቶች እየመጡ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የመዳረሻ ሀገራትን ከማስፋት በተጨማሪ በተለያዩ ዘርፎች የሠለጠኑ ባለሙያዎችን ለመላክ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ አሠራሮችን በማዘመን በወር እስከ 38 ሺህ ዜጎችን መላከ የሚቻለበት አሠራር ተፈጥሯል ብለዋል።
ከጀርመን የግል ኩባንያዎች ጋር በመነጋገርም የውጭ የሥራ ሥምሪት መስጠታቸውን ሚኒስትሯ ገልጸዋል።