ወንድማማችነት - የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ዋነኛ ምሰሶ

2 Mons Ago
ወንድማማችነት - የጠንካራ ሀገረ መንግሥት ምሥረታ ዋነኛ ምሰሶ

ወንድማማችነት በደም እና በአጥንት፣ በታሪክ፣ በሃይማኖት፣ በባህል እና በእሴት ከሚሊዮኖች ጋር በጥብቅ ያተሳስራል። ኅብረት፣ ማስተዋል እና ትጋት የወንድማማቾችን የዛሬ ኅልውና ብቻ ሳይሆን የነገ ዕጣ ፈንታንም ይወስናሉ።

ደስታ እና ኀዘን፣ ስኬት እና ውድቀት፣ ክብር እና ውርደት የአንድ ሀገር ዜጎች በጋራ የሚቀበሏቸው የሥራ ውጤቶች ናቸው።

በዐድዋ ድል ኮርቶ በ77 ድርቅ አብሬ መታወስ አልፈልግም ማለት የሚሆን አይደለም። “በተጋድሏችን ለጥቁር ሕዝቦች ነጻነት ብርሃን ፈንጥቀናል” እያሉ መነጋገር ባለመቻል እስካሁን ብረት ከማንሳት አዙሪት መውጣት አለመቻላችንን ከዓለም ልንሸሽገው አንችልም።

በሦስት ሺህ ዓመት ታሪክ፣ በቅርሳ ቅርሱ፣ በፊደሉ፣ በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ ሀብቱ አንገቱን ቀና የሚያደርግ ሁሉ፤ የስንዴ ምጽዋት ከሚያስከትለው አንገት መድፋት ሊድን አይችልም። የሀገር ልጅነት ተወደደም ተጠላም በበጎውም በክፉውም የተጋመደ ነው።

የወንድማማችነት ስሜት ሀገርን እንደ የጋራ ቤት፣ ሕዝቡንም እንደ ቤተሰብ የማየት የመተሳሳብ ስሜት ይፈጥራል። ይህ ስሜት እኛ እና እነሱ በሚል ከመከፋፈል ይልቅ በጎደለ የመሙላት ትብብርን ያጎለብታል።

የተባበረ ክንድ ደግሞ ጎባጣውን ያቀናል፣ ተራራውን ይደለድላል፣ በረሃውን ገነት ያደርጋል። ከሁሉም በላይ ግን የአንዱ መኖር ለሌላው የኅልውናው መሠረት እንጂ የስጋቱ ምንጭ አይሆንም።

የጋራ መኖሪያ ቤታችን ኢትዮጵያን ከዘር፣ ከሃይማኖት እና ከቋንቋ መቆራቆዝ ወጥተን በአንድነት ብናለማት ሁሉ ያለን፣ የታፈርን እና የተከበርን እንሆናለን።

ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው፤ በሐሳብ መለያየት እንኳን ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ውስጥ ይቅርና በቤተሰብ መካከልም ማስቀረት አይቻልም። ሰው ከራሱ ጋር እንኳን የማይስማማበት አልፍ ጉዳይ አለው።

ሐሳቡን ስላልተቀበለው ስለ ልጁ የማይገደው አባት፣ ምክሯን ስላልሰማች የልጇን ክፉ የምትመኝ እናት፣ በሐሳብ ስለተለያዩ እስከ መጠፋፋት የሚጨካከኑ እህት እና ወንድም ይኖሩ ይሆን?

ያለ ወንድማማችነት የሀገር ፍቅር ስሜት መፍጠር አይታሰብም። የሀገር ፍቅር የሌለው ዜጋ ደግሞ ከራሱ ጥቅም አሻግሮ እንደ ሕዝብ ማሰብ ይሳነዋል። ገንዘብ ካስገኘ በርበሬ ላይ ቀይ አፈር፣ ጤፍ ውስጥ ጀሶ፣ ማር ላይ ስኳር ሊጨምር ይችላል።

ለእንዲህ ዓይነቱ ዜጋ ዋጋ ለመጨመር ጤፍ እና ዘይት መደበቅ፣ ከሚዛን መስረቅ እና ከሸጠው ላይ የመንግሥትን ግብር መሰወር ቢዝነስ ነው።

የእኔነት ስሜት መፍጠር ያልቻለ ሀገር ከሚሠራ መንገድ ላይ ፌሮ የሚሰርቅ፣ የአስፋልት አካፋይ ብረት ገንጥሎ በኪሎ የሚሸጥ፣ ለጥቂት ፍርፋሪ ሲል ከሀገር ጠላቶች ጋር የሚያብር ትውልድ ይፈጥራል።

የሀገር ዳር ድንበር የሚጠበቀው በጦር መሣሪያ ብቻ የሚመስለው ካለ ተሳስቷል። ወንድማማችነት የጎደለው ሕዝብ የቱንም ያህል ቢታጠቅ የሀገሩን ጥቃት ሊመክት አይችልም። የሀገር ፍቅር ያለው ሕዝብ ወንድማማችነቱ ከመድፍ እና ከታንክ፣ ከጦር አውሮፕላንም ይበልጣል።

ኢትዮጵያዊያን ወንድማማች ሕዝቦች ለመሆናችን አስረጅ አይፈልግም። የሰሜኑ ሰው ከደቡቡ፣ የምሥራቁ ሰው ከምዕራቡ ተዋልዷል። ይህን ትሥሥር ዋጋ ከሰጠነው እንኳን ለራሳችን ለአፍሪካ ስንተርፍ በልዩነት ከተሰለፍን ግን ብዙ ሆነን የማንፈራ፣ አንዳች ሳይጎድለን እጅ የምንዘረጋ እንሆናለን።

ኢትዮጵያዊያን ሲተባበሩ የማይቻል የሚመስለውን ችለው አሳይተዋል። ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ምኞት ብቻ ሆኖ እንዲቀር ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለግንባታው የሚያስፈልገውን ብድር እና ድጋፍ ከመከልከል አንሥቶ፣ የታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት እስከ ወታደራዊ ማስፈራሪያ የደረሰ ያልተቋረጠ ጫና አሳድረዋል።

የኃያላኑ ሀገራት መንግሥታት “ግብጽ ግድቡን ልታፈነዳው ትችላለች” እስከ ማለት ሲወርዱ ዓለም አቀፍ መርሆችን ጠቅሶ “አግባብ አይደለም” ለማለት የደፈረም ብዙ አልነበረም።

በድርድሩ ሂደት የነበረው ኢ-ፍትሐዊ ዲፕሎማሲያዊ ጫናም የአደባባይ ምሥጢር ነው። አንድነት ከሌላ ዓለም 86 በመቶ በምታዋጣበት ውኃ ላይ ቀድተህ አትጠጣም እስከ ማለት የሚደርስ በደል ሊፈጽም እንደሚችል ይህ ኃያው ማሳያ ሆኖ አልፏል። ሆኖም ኢትዮጵያዊያን የራሳቸውን አቅም አስተባብረው ፈተናዎችን ሁሉ አልፈው ግድቡን ከጫፍ እስከ ማድረስ ፀንተዋል።

የዐድዋ ድል ሁነኛ ስትራቴጂም ወንድማማችነት ነበር። ወንድማማቾች ለሀገራቸው፣ ለእምነታቸው እና ለትዳራቸው ሲሉ ከሁሉም የሀገሪቱ ጫፍ በአንድነት ዐድዋ ላይ ስለ ነፃነት ተፋልመው ለመላው የጥቁር ሕዝብ ያለመገዛት ብርታት ሰንቀዋል።

በወንድማማችነት ስሜት ሀገር እንገንባ!

በኢዮብ መንግሥቱ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top