በሩብ ዓመቱ ከሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት 685 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኘ

7 Mons Ago
በሩብ ዓመቱ ከሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት 685 ሚሊዮን ብር ገቢ ተገኘ

በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራት ከ411 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች አገልግሎት በመስጠት 685 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አስታወቀ።

የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዳጋቶ ኩምቤ እንደገለጹት፤ የተቋሙን የአገልግሎት አሰጣጥና የክፍያ ሥርዓት ከኢትዮ-ቴሌኮምና ከሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ እንዲሆን ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

በዚህም 293ሺህ ጉዳዮችን በዲጂታል መተግበሪያ በማረጋገጥ እንደመዘገበና ከእነዚህም መካከል የሚንቀሳቀስና የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውልና የብድር ውሎች ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራት ከ411 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች አገልግሎት በመስጠት 685 ሚሊየን ብር ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ተቋሙ አሠራሩን በማዘመኑ በሩብ ዓመቱ የዕቅዱን 147 በመቶ ማሳካት መቻሉንም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያስረዱት፡፡

ከተገኘው ገቢ የመኪና ሽያጭ እና የባንክ ብድር ውል አብዛኛውን መጠን እንደሚይዝ አመላክተዋል።

የሚሰጡትን አገልግሎቶች ከወረቀትና ከሰው ንክኪ የፀዳ ማድረግ መቻሉ ለደንበኞች ፈጣንና ዘመናዊ አገልግሎት መስጠት እንዳስቻላቸው ዋና ዳይሬክተሩ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ተቋሙ የሚሰጠው አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጠንም ሆነ በጥራት እያደገ መምጣቱን ተከትሎ የሚሰበሰበው የአገልግሎት ክፍያ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት 2 ቢሊየን ብር ገቢ ከአገልግሎት ክፍያ ለማግኘት ዕቅድ መያዙንም ገልፀዋል።

የኢ-ሰርቪስ አገልግሎት መጀመሩ፣ በሠራተኞች ዘንድ የአገልጋይነትና የተጠያቂነት አሠራር መስፈኑ የተገልጋዮችን እርካታ ከፍ ከማድረግ ባለፈ የተቋሙ ገቢ እንዲጨምር ማስቻሉንም ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በርካታ ዜጎች በሕጋዊ ውልና ማስረጃ መገልገል መጀመራቸው ለአፈጻጸሙ መጨመር ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top