የአሜሪካ ጦር መከርብ ቀይ ባሕር ላይ ከየመን የተተኮሱ ድሮኖችን መትቶ መጣሉን ገለጸ

7 Mons Ago
የአሜሪካ ጦር መከርብ ቀይ ባሕር ላይ ከየመን የተተኮሱ ድሮኖችን መትቶ መጣሉን ገለጸ
ፎቶ - ፋይል

የአሜሪካ ጦር መርከብ ሦስት ድሮኖችን ቀይ ባሕር ላይ መትቶ መጣሉን የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ ገልጿል።

ድሮኖቹ ሦስቱ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲቃጡ ነው የአሜሪካ ጦር መከርብ እርምጃውን የወሰደው።

ሁለት የንግድ መርከቦች በሚሳዔል ቢመቱም የተጎዳ ሰው ግን የለም ሲል ማዕከላዊ ዕዙ ገልጿል።

ከ14 ሀገራት ጋር ግንኙነት ያለው ‘ዩኤስኤስ ካርኒ’ የተሰኘው የጦር መርከብ እሑድ ዕለት በኢራን ከሚደገፉት የየመን ሁቲ አማፂያን ጋር ሲዋጋ መዋሉ ተሰምቷል።

የሁቲ አማፂያን ቃል አቀባይ ሁለት የእስራኤል መርከቦች ከቡድኑ ባሕር ኃይል ጥቃት እንደደረሰባቸው አሳውቀዋል።

በኢራን የሚደገፉት የሁቲ ታጣቂዎች በአውሮፓውያኑ 2014 መንግሥት ተገልብጦ የእርስ በርስ ጦርነት ከተከሰተ ጀምሮ አንዳንድ የሀገሪቱን ክፍሎች ተቆጣጥረው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።

ቡድኑ በተለይ ደግሞ በቅርቡ ከተቀሰቀሰው የእስራኤል ሐማስ ጦርነት በኋላ ቀይ ባሕር ላይ የሚንቀሳቀሱ የእስራኤል መርከቦችን ዒላማ እያደረገ ይገኛል።

የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ዕዝ እንደገለጠው እሑድ ጥዋት ‘ዩኤስኤስ ካርኒ’ ፀረ-መርከብ ባሌስቲክ ሚሳዔል ‘ዩኒቲ ኤክስፕሎረር’ ወደተሰኘ የዩናይትድ ኪንግደም የንግድ መርከብ ተተኩሷል።

ከዚህ ጥቃት በኋላ ሌላ ድሮን ወደ ጦር መርከቡ ቢሰነዘርም ሊያከሽፍ መቻሉን ያሳወቀው ዕዙ፣ ጥቃቱ የአሜሪካ ጦር መርከብን ዒላማ ስለማድረጉ ግን እርግጠኛ አይደለንም ብሏል።

በተመሳሳይ ቀን ከሰዓት ‘ዩኒቲ ኤክስፕሎረር’ ከሁቲ ቁጥጥር ሥር ከሚገኝ ሥፍራ በተተኮሰ ሚሳዔል ተመትቶ አነስተኛ ጉዳት ደርሶበታል።

የአሜሪካ ጦር መርከብ ሌላ የድሮን ጥቃት እንደተሰነዘረ ከተገነዘበ በኋላ ጥቃቱ ጉዳት ከማድረሱ በፊት መትቶ እንደጣለው ተነግሯል።

ከዚህ ጥቃት በኋላ ደግሞ ሁለት የፓናማ ባንዲራ የሰቀሉ መርከቦች በሚሳዔል ጥቃት እንደተመቱ ተዘግቧል። ‘ዩኤስኤስ ካርኒ’ እኒህን መከርቦች ለመርዳት እየሄደ ሳለ ሌላ የድሮን ጥቃት ተሰንዝሮ እሱንም ማክሸፉን አሳውቋል።

ማዕከላዊው ዕዝ እንዳለው ጥቃቶቹ መርከቦቹ ላይ የሚሠሩ የበርካታ ሀገራት ዜጎችን “ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል” ይህ ደግሞ “ለዓለም አቀፍ ንግድና የባሕር ጉዞ ስጋት ነው።”

“አልፎም እኒህ ጥቃቶች የመን ከሚገኙ ሁቲዎች ይሰንዘሩ እንጂ በኢራን እየተደገፉ እንዳለ እናምናለን” ብሏል።

“ዩናይትድ ስቴትስ ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር በመሆን ተመጣጣኝ ምላሽ እንደምትሰጥ ልንገልጥ እንወዳለን።” ሲልም ማከሉን ቢቢሲ ዘግቧል።

በያዝነው ሳምንት መባቻ አሜሪካ፤ ከእስራኤል ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ መርከቦች ላይ ጥቃት ያደረሱ ታጣቂዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ገልጣ ነበር።

ሁቲዎች ራሳቸውን በኢራን ከሚደገፉ ቡድኖች ጋር “የተቃውሞ ዘንግ” ብለው የሚጠሩ ሲሆን እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና መላው የምዕራቡ ዓለምን የሚቃወሙ ናቸው።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top