ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት የደርባኑ BRICS+ ስብሰባ እንደ ሀገር ለሚጠበቅብን ሥራ መሠረት የጣለ ነው፦ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ

2 Mons Ago
ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት የደርባኑ BRICS+ ስብሰባ እንደ ሀገር ለሚጠበቅብን ሥራ መሠረት የጣለ ነው፦ በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ

ኢትዮጵያ የተሳተፈችበት የደርባኑ BRICS+ ስብሰባ እንደ ሀገር ለሚጠበቅብን ሥራ መሠረት የጣለ መድረክ ነው ሲል በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታወቀ።

እ.አ.አ ታኅሣሥ 2 እና 3 ቀን 2023 በደርባን ከተማ የተካሄደው መድረክ ደቡብ አፍሪካ የ2023 ፕሬዚዳትነት ኃላፊነቷን የምታጠናቅቅበት እና የቀጣይ ዓመት ፕሬዚዳንትነቱን ለምትቀበለው ሀገር የምታስተላልፍበት ነበር።

እንዲሁም ወደ ትብብሩ የተቀላቀሉ አዲስ አባል ሀገራት ስለትብብሩ አሠራር እና አጀንዳዎች በዝርዝር የመከሩበት መድረክ እንደነበርም ተጠቅሷል።

በስብሰባው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እና የትብብሩ የበላይ ኃላፊ (BRICS ETHIOPIA SHERPA) አቶ ማሞ ምሕረቱ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ተሳትፏል።

የልዑካን ቡድኑ ከውጭ ጉዳይ የሚመለከታቸው የሥራ ክፍል ኃላፊዎች እና በደቡብ አፍሪካ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ዶ/ር ሙክታር ከድር ተካትተዋል።

ልዑካን ቡድኑ ከትብብር መድረኩ ጎን ለጎን ከሩሲያ፣ ከቻይና፣ ከሕንድ እና ከደቡብ አፍሪካ ሀገራት ልዑካን ቡድኖች ጋር በBRICS+ ዝርዝር አሠራር እንዲሁም በሁለትዮሽ የልማት እና ፋይናንስ ትብብር መሰኮች ዙሪያ ገንቢ እና ጠቃሚ ውይይቶችን አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ ከBRICS+ ትብብሩ ልታሳካ የምትፈልገውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም፣ ዓለም አቀፍ የባለብዙ መድረክ ፍትሐዊነት ሰለሚሻሻልበት እና ለደቡብ ደቡብ ትብብር አጋዥ ሚና ለመጫወት ዝግጁነቷን ማስገንዘብ ተችሏል።

ለቀጣይ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ለሚጠበቅባት ሥራ መሠረት የጣለ መድረክ ሆኖ በድል መጠናቀቁን ኤምባሲው አስታውቋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top