በኢራቅ በሚገኝ የአሜሪካ የጦር መንደር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በዝግጅት ላይ የነበሩ አምስት ተዋጊዎች ተገደሉ

2 Mons Ago
በኢራቅ በሚገኝ የአሜሪካ የጦር መንደር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በዝግጅት ላይ የነበሩ አምስት ተዋጊዎች ተገደሉ
ፎቶ - ፋይል

በሰሜን ኢራቅ በምትገኝ ኪርኩክ ከተማ ውስጥ በሚገኝ የአሜሪካ የጦር መንደር ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ፈንጂዎችን ሲያዘጋጁ የነበሩ አምስት የኢራቅ ታጣቂዎች አሜሪካ በወሰደችው የአየር ጥቃት መገደላቸው ተገለጸ።

ጥቃቱ መፈፀሙን ያረጋገጡት ሦስት የኢራቅ የፀጥታ ምንጮች ለሬውተርስ እንደገለጹት፣ በጥቃቱ የተገደሉት ታጣቂዎች በኢራን የሚደገፉ ሚሊሺያ አባላት ናቸው።

አንድ የአሜሪካ ወታደራዊ ኃላፊ በበኩላቸው፣ በኪርኩክ በሚገኝ የድሮን ሳይት ላይ ሊደርስ ከነበረ እርግጠኛ ጥቃት ራስን የመከላከል እርምጃ መወሰዱን አረጋግጠዋል።

ከቴህራን ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያላቸውን የተለያዩ የኢራቅ ታጣቂ ኃይሎችን በአንድ ጥላ ሥር እንዳሰባሰበ የሚነገርለት ‘ኢስላሚክ ሬዚስታንስ ኢን ኢራቅ” የተባለ ኃይል ባወጣው መግለጫ፣ አምስት አባላቱ መገደላቸውን ገልጾ፣ ለዚህም በአሜሪካ ወታደሮች ላይ የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ ዝቷል።

እስራኤል በጋዛ ላይ ለምትፈፅመው የቦምብ ጥቃት ዋሽንግተን ድጋፍ እየሰጠች ነው የሚሉ የኢራቅ ታጣቂ ኃይሎች ይህንኑ ለመበቀል እ.አ.አ ከጥቅምት 17 ቀን 2023 ጀምሮ ከ70 በሚበልጡ የአሜሪካ ይዞታዎች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተናግረዋል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል። 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top