የጆርጅ ፍሎይድን ገዳይ በጩቤ የወጋው እስረኛ በመግደል ሙከራ ተጨማሪ ክስ ተመሰረተበት

1 Yr Ago 268
የጆርጅ ፍሎይድን ገዳይ በጩቤ የወጋው እስረኛ በመግደል ሙከራ ተጨማሪ ክስ ተመሰረተበት

ጥቃቱ የተፈፀመው ባለፈው ወር በሀገረ አሜሪካ በአሪዞና ግዛት በታክሰን ከተማ በሚገኝ አንድ የፌደራል ማረሚያ ተቋም ውስጥ ነው።

በማረሚያ ተቋሙ የሕግ ላይብረሪ ውስጥ ጆን ተርስካክ የተባለው እስረኛ የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ገዳይ የቀድሞ ፖሊስ መኮንን ዴሪክ ሾቪንን 22 ጊዜ በጩቤ ወጋግቶ ክፉኛ እንዳቆሰለው አልጀዚራ ዘግቧል።

በዚህም የቀድሞው የወንጀል ቡድን አባል እና የ30 ዓመት ፍርደኛው ጆን ተርስካክ አሁን ደግሞ በመግደል ሙከራ እና ሌሎች ተጨማሪ ወንጀሎች ሌላ ክስ ተመስርቶበታል።

ጥቃቱን ከአንድ ወር አስቀድሞ ሆን ብሎ አቅዶ መፈፀሙን ጆን ተርስካክ ለመርማሪዎች ገልጿል።

ጥቃቱንም የ‘ታንክስ ጊቪንግ’ የምሥጋና ክብረ በዓልን ተከትሎ በዋለው ‘ብላክ ፍራይዴይ’ መፈፀሙን እና ይህን ያደረገውም ሆን ብሎ በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ማግስት የነበረውን ፀረ የዘር ጥቃት ንቅናቄ ለማስታወስ መሆኑን ገልጿል።

በጆርጅ ፍሎይድ ግድያ 22 ዓመት ተኩል ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኘው የቀድሞ ፖሊስ መኮንን ዴሪክ ሾቪን ከደረሰበት ጉዳት እንደሚያገግም ይጠበቃል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top