"ኤች.አይ.ቪ ምን እንደሆነ የማያውቅ ትውልድ እየተፈጠረ ነው" - ዶ/ር ወንድወሰን አሞኘ

9 Mons Ago 394
"ኤች.አይ.ቪ ምን እንደሆነ የማያውቅ ትውልድ እየተፈጠረ ነው" - ዶ/ር ወንድወሰን አሞኘ

የኤች.ኤይ.ቪ ኤድስ ቀን በመላ ሃገሪቱ “የማህበረሰብ መሪነት ለላቀ ኤች.አይ.ቪ መከላከል” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ይገኛል፡፡ ይህን በማስመልከት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ወንድወሰን አሞኘ ከኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

በቆይታቸውም በሽታው በዓለም አቀፍ ደረጃ በ1974 ዓ.ም በኢትዮጵያ ደግሞ ከአምስት ዓመት በኋላ በ1978 ዓ.ም መከሰቱን አስታውሰው፤ በወቅቱ ከፍተኛ የሆነ ድንጋጤ እና ፍርሃት ተፈጥሮ የነበር ቢሆንም ማህረሰቡን ስለበሽታው የማስረዳት እና ግልፅ የማድረግ ሂደቱ የተሳካ ነበር ሲሉ አስታውሰዋል፡፡

አሁን ላይ በቴክኖሎጂ እና በተለያዩ ሁኔታዎች የዘመንን ቢሆንም በሽታው በተለይም በዋናነት የአምራች ሃይል የሆነውን ወጣቱን ሃይል ዒላማው አድርጎ ውስጥ ለውስጥ እያጠቃ ይገኛል ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ባለፉት አራት አስርት ዓመታት ለበሽታው ስናደርገው የነበረው እንቅስቃሴ እየተዳከመ መጥቷል ያሉት ዶ/ር ወንድወሰን  በሽታው ግን መግደሉን እንዳልቀነሰ አመላክተዋል፡፡

ዶ/ር ወንድወሰን አክለውም አሁን ላይ ስለ በሽታው ስም ብሎም ምንነት የማያውቅ ትውልድ እየመጣ ነው ያሉ ሲሆን፤ ይህም በዝምታ እንድንሞት እና የተጠቂ ቁጥር እንዲያሻቅብ ያዳረገው አንዱ ምክንያት ነው ሲሉም ያነሳሉ፡፡

እንደ መጀመሪያ በሽታውን ለመከላከል እና በበሽታው የተጠቁ የማህበረሰብ ክፍሎች የስነልቦናዊ ጫና እንዳይደርስባቸው የማስተማር፤ ብሎም በሚዲያ ይሰሩ የነበሩ የግንዛቤ ስራዎች መዳከማቸው ማህረሰቡ በሽታው የለም ብሎ እንዲስብ ማደረጉን ያስረዳሉ፡፡ 

በመሆኑ አሁን ላይ ማህበረሰቡ ጋር መድረስ በሚቻልባቸው ሁሉንም መንገዶች በመጠቀም የተጠቂ ቁጥርን መቀነስ ላይ ሊሰራ ይገባል በማለት ይጠቁማሉ፡፡

በሃገራችን በቀደመው ግዜ ለመጠንቀቂያ ይረዱ የነበር ቁሶቁች በርካሽ አለፍ ሲልም በነፃ ይገኙ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ላይም ከመድሃኒት ባልተናነሰ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶ በሽታውን ለመከላከል የሚረዱ ቁሶቁች ዜጎች መግዛት በሚችሉት ዋጋ ሊቀርቡ ይገባል ሲሉ ይመክራሉ፡፡

ይህን መሰል ትውልድ ቀጣፊ ወረርሽኝ ለመከላከል ኃላፊነቱ ወደ አንድ አካል ብቻ በመግፋት ሊተው አይገባም ያሉት ዶ/ር ወንድወሰን፤ መንግስት እና ማህበረሰቡ በጋራ በመሆን የተሻለ ነገን ማየት ላይ ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ያሳስባሉ፡፡

በአፎምያ ክበበው


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top