ኢትዮጵያ በኮፕ28 'ግሪን ዞን' ያዘጋጀችው የአረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ (ፓቪሊዮን) የመሪነትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው: - አሁና ኢዚያኮንዋ

7 Mons Ago
ኢትዮጵያ በኮፕ28 'ግሪን ዞን' ያዘጋጀችው የአረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ (ፓቪሊዮን) የመሪነትን ቁርጠኝነት ያሳየ ነው: - አሁና ኢዚያኮንዋ
ኢትዮጵያ በኮፕ28 'ግሪን ዞን' የዱባይ ከተማ ኤክስፖ ላይ ያዘጋጀችው የአረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ(ፓቪሊዮን) የሚደነቅ እና በዋናነት የመሪነትን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ቀጣናዊ ዳይሬክተር አሁና ኢዚያኮንዋ ገለጹ።
 
አሁና ኢዚያኮንዋ በኮፕ28 'ግሪን ዞን' የዱባይ ከተማ ኤክስፖ ላይ የተዘጋጀውን የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ(ፓቪሊዮን) ጎብኝተዋል።
 
በአውደ ርዕዩ እስካሁን ያልተነገረና ትልቅ ታሪክ የተመለከቱበት መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ ወቅቱ ተግባርን የሚጠይቅ በመሆኑ ለተግባሩ የሚያስፈልገውን ገንዘብ መመደብ ይገባናል ብለዋል።
 
ኢትዮጵያ ያዘጋጀችው የአረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ (ፓቪሊዮን) አስደናቂ ተግባርን የሚያሳይ እና ሁሉም ወደ ተግባር መግባት እንዳለበት ያመላከተ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ይህም ተግባሩ በአንዲት አፍሪካዊት ሀገር ላይ መጀመሩን ያመላከተ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
 
ዳይሬክተሯ "እኔ በዚህ ቦታ ላይ የተመለከትኩት ቁርጠኝነት ነው፤ ይህም በግንባር ቀደምትነት የመሪነት ቁርጠኝነትን ያሳየ ነው" ሲሉም መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
 
በኮፕ28 'ግሪን ዞን' የዱባይ ከተማ ኤክስፖ ላይ የተዘጋጀውን የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ዐሻራ መካነ ርዕይ(ፓቪሊዮን) በተለያዩ ሀገራትና ተቋማት መሪዎች እየተጎበኘ ይገኛል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top