መቐለ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ሚኒስቴር የተመደቡለትን ከ1 ሺህ በላይ አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር መዘጋጀቱን አስታውቋል።
የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዶክተር ትካቦ ገብረስላሴ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከህዳር 28 እስከ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ባሉት ቀናት አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት አድርጓል።
“ዩኒቨርሲቲው አዲሀቂን ጨምሮ በሁለት ጊቢዎቹ ተማሪዎቹን በመቀበል በማህበራዊና በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፎች ለማስተማር ተዘጋጅቷል” ብለዋል።
የመማሪያ፣ መመገቢያና ማደሪያ ክፍሎች ጨምሮ በጊቢ ጽዳትና በአረንጓዴ ስፍራዎች ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰዋል።
የተገኘው ሰላም የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም አሁን ላይ ነባር ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ መሆኑን አመልክተዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ሳምንት 2ሺህ 35 ተማሪዎችን በአንደኛ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ማስመረቁን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል።