''ፆታዊ ጥቃትን መቼም፣ የትም፣ በምንም ዝም አንልም'' በሚል መሪ ሀሳብ የነጭ ሪቫን ቀንና የፆታዊ ጥቃት ማስቆሚያ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ የኢፌዴሪ ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት በአዳማ ተካሄዷል።
ፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ወቅት ፆታዊ ጥቃት በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚያሳድረው የስነ-ልቦና፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ለቀጣይ 16 ቀናት የሚካሄደው ንቅናቄ በየደረጃው ያሉ የባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡ ያግዛል ብለዋል።
በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በስራ ቦታ የሴቶችና እናቶችን ጫና ለመቀነስ የህፃናት ማቆያ መገንባት፣ ህይወታቸው እንዲሻሻል የገቢ ምንጭና ሌሎች ተጠቃሚነታቸውን የሚያሳድጉ ስራዎች ትኩረት ሊያገኙ እንደሚገባም ገልጸዋል።
''ችግሩን በቀላሉ ማየት የለብንም'' ያሉት ፕሬዚዳንቷ ሴቶች፣ ህፃናትና እናቶችን ከወደቁበት የማንሳትና ስነ-ልቦናቸውን የመገንባት ስራ ተገቢውን ትኩረት እንዲያገኝም አሳስበዋል።
የፆታዊ ጥቃትን ለማስቆም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት እንደሚገባና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበው እንደ አገር በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስረድተዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ፆታዊ ጥቃት በሴቶች ላይ የስነ-ልቦና ጫና ከማሳደር ባለፈ ለውስብስብ ችግሮች ይዳርጋቸዋል ብለዋል።
ችግሩን በመከላከል የጤና፣ የስነ-ልቦና ጉዳትን ጨምሮ የሚደርስባቸውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር መግታት ይገባል ነው ያሉት።
በሚኒስቴሩ አስተባባሪነት ተጎጂዎች ጥቆማ የሚሰጡበት አድራሻ፣ የህግ፣ የምርመራና የህክምና፣ ጊዜያዊ ማረፊያና ማገገሚያ እንዲሁም የስነ-ልቦናና የመልሶ ማቋቋም ስራ በስፋት መሰራቱን አንስተዋል።
ሴቶችና ህፃናትን ከማንኛውም ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል ሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተደድር አመራሮችና ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
ከመረጃ እጥረትና ከህግ ክፍተት አኳያ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ጠቅሰው ችግሮቹን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቀጣይ በትኩረት ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።