"ያለ ምግብ ግማሽ ክፍለ ዘመን ቆይቻለሁ" ያሉት ቬትናማዊት አዛውንት ዓለምን እያነጋገሩ ነው

7 Mons Ago
"ያለ ምግብ ግማሽ ክፍለ ዘመን ቆይቻለሁ" ያሉት ቬትናማዊት አዛውንት ዓለምን እያነጋገሩ ነው
"ያለ ምግብ ግማሽ ክፍለ ዘመን ቆይቻለሁ" ያሉት የ75 ዓመቷ ቬትናማዊት አዛውንት ዓለምን በማነጋገር ላይ ይገኛሉ፡፡
 
አዛውንቷ ያለ ምግብ 50 ዓመት የኖሩት ውኃ እና የለስላሳ መጠጦችን ብቻ በመጠቀም መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
 
ቡ ታይ ሎይ የተባሉት እኚህ አዛውንት ምግብ የማቆም ውሳኔያቸው መነሻ እ.አ.አ በ1963 ካጋጠማቸው አደጋ ጋር እንደሚገናኝም የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ያስረዳል፡፡
 
ነገሩ እንዲህ ነው - በቬትናም ጦርነት ወቅት እርሳቸው እና ባልደረቦቻቸው ቁሰለኛ ወታደሮችን ለማከም በየቦታው ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡
 
በአንዱ እለት ተራራ እየወጡ ሳለ መብረቅ ይመታቸው እና የህመሙ ስሜት ለቀናት ምግብ ይከለክላቸዋል፡፡
 
በዚህም ጓደኞቻቸው የሸንኮራ አገዳ ጭማቂ እየመላለሱ ያጠጧቸው እንደነበር ይተርካሉ፡፡
 
ከህመማቸው ካገገሙ በኃላ በወዳጅ ዘመድ ተግሳጽ እንደነገሩ ምግብ ይቀማምሱ እንደነበር የሚያስታውሱት ቡ ታይ ሎይ እ.አ.አ ከ1970 ጀምሮ ግን የምግብ ዘር ከአፋቸው ደርሶ እንደማያውቅ ይልቁንም ውኃ እና ለስላስ ብቻ እንደሚጠቀሙ ይገልጻሉ፡፡
 
 
“የምግብ ሽታ ጤናዬን ያናጋዋል” የሚሉት አዛውንቷ ለልጆቻቸው ምግብ ያበስሉ በነበረበት ጊዜም ምግቡን ቀምሰው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡
 
ለስላሳ መጠጦች ሰውነት የሚያስፈልገውን ኃይል በፍጥነት የመተካት እና ለስርዓተ ልመት ጠቀሜታ ቢኖራቸውም በተደጋጋሚ ሲወሰዱ በርካታ የጤና ችግር ሊያስከትሉ እንደሚችሉ የጤና ባለሞያዎች ይናገራሉ፡፡
 
በቬትናም እንደነዚህ ያሉ ወጣ አግራሞት የሚፈጥሩ መረጃዎችን መስማት አዲስ ነገር አይደለም ይላል የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ።
 
በጎርጎሮሳውያኑ የዘመን ቀመር 2023 መግቢያ ላይ ታይ ንጎክ የሚባሉ የ80 ዓመት አርሶ አደር "ለ60 ዓመት እንቅልፍ አልተኛሁም" ብለው መናገራቸው በወቅቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡
 
ሁለቱም ጉዳዮች በሳይንሳዊ መንገድ ማረጋገጫ ያልተደረገባቸውና በዓይን እማኞች ምስክርነት ብቻ የተደገፉ መሆናቸውን ዘገባው አበክሯል፡፡
 
በቪየትናም የአንድ ሰው አማካይ የመኖር እድሜ 75 ዓመት መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
 
ጊነስ የዓለም ድንቃ ድንቅ መዝገቦች እ.አ.አ በ1981 ስኮትላንዳዊውን አግነስ ባርቢዬሪን ውኃና የተለያዩ ፈሳሾችን ብቻ በመጠቀም ምግብ ሳይበላ ለ382 ቀናት የቆየ የመጀመሪያው ሰው በማለት በክብረ ወሰንነት መዝግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top