የምስራቅ አፍሪካ የፍትሕ ፍርድ ቤት በፊርማ ማሰባሰብ በ4 ቢሊዮን ዶላር በዩጋንዳ እና ታንዛንያ መካከል የሚገነባው የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር እንዲቆም የቀረበለትን ጥያቄ ውድቅ አድርጓል፡፡
ኔቸር ጀስቲስ የተባለ እና ሌሎች ሶስት የሲቪክ ማህበረሰብ ተቋማት የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩ ግንባታ እንዲቆም ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ ያስገቡት እ.አ.አ በ2020 ነበር።
ፍርድ ቤቱ የግንባታው ይቁም ጥያቄው "የማቅረቢያ ጊዜው የዘገየ እና ጉዳዩ ከሱ የሕጋዊነት ወሰን በላይ በመሆኑ" እንዳልተቀበለው ረቡዕ ባስተላለፈው ውሳኔ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል።
1 ሺህ 443 ኪሎ ሜትር የሚረዝመው እና የምስራቅ አፍሪካ የድፍድፍ ነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር የሚል ስያሜ ያለው ፕሮጀክቱ የዩጋንዳ እና ታንዛንያ መንግስታት ከቶታል ኢነርጂስ እና ሲኤንኦኦሲ ከተሰኘ የቻይና ኩባንያ ጋር እያስገነቡት ያለ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
ውሳኔው በከባቢ አየር ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት እንዲቀጥል የሚፈቅድ ነው ሲሉ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ተችተውታል።
ተሟጋቾቹ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁ መግለጻቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል።