ተሳፋሪ መስለው በመግባት አሽከርካሪውን የገደሉ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

7 Mons Ago
ተሳፋሪ መስለው በመግባት አሽከርካሪውን የገደሉ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ
 
 
የትራንስፖርት ተጠቃሚ መስለው ተሽከርካሪ ውስጥ በመግባት እና ንብረት ለመውሰድ በማሰብ በሾፌሩ ላይ የውንብድና ወንጀል ፈፅመው ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረጉ ሁለት ግለሰቦች በፅኑ እስራት ተቀጥተዋል፡፡
 
ዮሃንስ ሰለሞን እና እዮብ በሃይሉ የተባሉት ተከሳሾች ወንጀሉን የፈፀሙት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው ሳሪስ አቦ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡
 
ተከሳሾቹ ዛይራይድ ወደተባለ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ድርጅት ስልክ በመደወል ተሽከርካሪ እንዲመጣላቸው ካደረጉ በኋላ ከሳሪስ አቦ ወደ ጎተራ ከኋላ ወንበር ተቀምጠው ጉዞ ይጀምራሉ፡፡
 
ነገር ግን ጎተራ ከደረሱ በኋላ ምክንያት ፈጥረው በድጋሚ ወደመጡበት እንዲመልሳቸው ለአሽከርካሪው ይነግሩትና ወደ ሳሪስ አቦ ይመለሳሉ፡፡
 
ዮሃንስ ሰለሞን እና እዮብ በሃይሉ ያሰቡትን ወንጀል ለመፈፀም የሚያስችላቸውን ጨለማ እና ሰዋራ ስፍራ ሲያገኙ እዮብ በሃይሉ የአሽከርካሪውን አንገት በገመድ ሲያንቀው ዮሃንስ ሰለሞን ደግሞ በድብቅ ይዞት በነበረው መዶሻ አናቱን በመምታት ህይወቱ እንዲያልፍ አድርገዋል፡፡
 
የአሽከርካሪውን መሞት ካረጋገጡ በኋላ ተሽከርካሪውን ጨምሮ ሁለት ሞባይል ስልኮችን እና ጥሬ ገንዘብ የወሰዱት ተከሳሾቹ ፤ መኪናውን ለመሸጥ ሞክረው አልሳካ ሲላቸው ወርቁ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ መንገድ ዳር አቁመው ተሰውረዋል፡፡
 
የአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀሉ እንደተፈፀመ ሪፖርት ከደረሰው በኋላ የምርመራ እና የክትትል ቡድን በማቋቋም ባደረገው ከፍተኛ ጥረት ተከሳሾቹ ከሶስት ወራት ፍለጋ በኋላ በቁጥጥር ስር ሊውሉ ችለዋል፡፡
 
ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድቤት ልደታ ምድብ 1ኛ ወንጀል ችሎት ሰሞኑን በዋለው ችሎት ተከሳሾቹ በፈፀሙት ከባድ የውንብድና ወንጀል ጥፋተኝነታቸውን በሰው እና በሰነድ ማስረጃ ካረጋገጠ በኋላ ዮሃንስ ሰለሞን በ15 ዓመት እንዲሁም እዮብ በሃይሉ በ12 ዓመት ፅኑ እስራ እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
 
የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ እና ተጠቃሚ በመምሰል በሾፌሮችም ሆነ በተሳፋሪዎች ላይ የሚፈፀሙ ተመሳሳይ ወንጀሎችን ለመከላከል ተገቢውን ትኩረት መስጠትና ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ እያሳሰበ በዚህ ወንጀል ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ሲያጋጥሙ ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን ያቀርባል፡፡
 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top