የዘንድሮው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP28) በዱባይ አዘጋጅነት ከዛሬው ጀምሮ መካሄድ ጀምሯል።
ለሚቀጥሉት 14 ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ ላይ የአየር ንብረት ለውጥ እያስከተላቸው ባሉት ጉዳዮች ላይ ውይይት ተድርጎ የውሳኔ ሀሳቦች ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል።
ጉባኤው ዲካርቦናይዜሽን፣ ዜሮ ልቀት እና የኃይል ሽግግርን በተመለከቱ አጀንዳዎች ላይ ውይይት የሚያደረግ ሲሆን፣ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል አዳዲስ የፋይናንስ ምንጮችን ማፈላለግን ጨምሮ ቅድሚያ የሚሰጡ እርምጃዎች ላይ ውሳኔ ይሰጣል።
በጉባኤው ላይ ከመንግሥታት፣ ከንግድ ተቋማት፣ ከኢንዱስትሪዎች፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ከሲቪል ማኅበረሰብ የተውጣጡ ተወካዮች ተገኝተዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን መንስኤዎችን ለመቅረፍ እና እየጨመረ የመጣው ሙቀት የሚያስከትላቸውን ተፅእኖዎች ለማስተካከል የሚያስችሉ አራት ጭብጦች ላይ ውይይት እንደሚደረግ የጉባኤው አጀንዳ ያመለክታል።
የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በቅርብ ጊዜ እንዳወጣው ሪፖርት የአየር ንብረት ለውጥ ከ10 የምድራችን ስጋቶች መካከል አንዱ ሆኗል።
ብሔራዊ የውቅያኖስ እና የከባቢ አየር አስተዳደር (NOAA) ባጠናከረው መረጃ በዚህ ዓመት በምድራችን እጅግ ሞቃታማ የሆነ መስከረም ተመዝግቧል። ‘NOAA’ እ.አ.አ በ2023 የፕላኔታችን የሙቀት መጠን እስከ ዛሬ ከተመዘገቡት የሙቀት መጠን ሁሉ ከፍተኛ እንደሆነ እና ይህ ደግሞ በታሪክ ከተመዘገቡት ሁሉ እጅግ ሞቃታማ ዓመት ሆኖ የማለፍ አጋጣሚ እንደሆነ ገልጿል።
"የዓለም ሙቀት በተከታታይ ከፍተኛ ሲሆን መስከረም 2023 በታሪክ አራተኛው ነው" ያሉት የ‘NOAA’ ዋና ሳይንቲስት ዶክተር ሣራ ካፕኒክ፣ "ይህ ወቅት በታሪክ ከተመዘገቡት ሁሉ እጅግ ሞቃታማ የሆነው መስከረም ብቻ ሳይሆን የአየር ንብረት ምዝገባ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ በ174 ዓመታት ውስጥ በጣም ሞቃታማ የሆነ ወር ነበር፤ የዚህ ዓመት መስከረም እ.አ.አ ከ2001-2010 ባሉት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከነበረው አማካይ የሐምሌ ወር ሙቀት ይበልጣል" በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ገልጸዋል።
በዚህ ጉባኤ የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤዎች ለመቅረፍ እና የፕላኔታችንን ሙቀት ለማስተካከል አራት አፋጣኝ ጉዳዮች ማለትም ቴክኖሎጂ እና ፈጠራ፣ አካታችነት፣ ግንባር ቀደም ማኅበረሰብ እና ፋይናንስ ላይ ትኩረት እንደሚደርግ አጀንዳው ላይ ተመላክቷል።
የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች የኢንዱስትሪ እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እና የጉባኤው (COP28) ሊቀመንበር ሱልጣን አህመድ አል ጃቢር (ዶ/ር)፣ ሀገራቸው የምታዘጋጀውን የዘንድሮ ጉባኤ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት እ.አ.አ በ2015 ፈረንሳይ ፓሪስ በተካሄደው 21ኛው የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (COP21) በ2050 የዓለምን ሙቀት ከኢንዱስትሪ በፊት ከነበረው የሙቀት መጠን ጋር ሲነፃፀር በ1.5°C ለመገደብ ስምምነት ተደርሶ እንደነበረ አስታውሰዋል።
ግቡን ለማሳካትም በ2030 ዓ.ም. የካርቦን ልቀትን በግማሽ መቀነስ እንዳለበት ስምምነቱ ላይ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ ግብ ለመድረስ 7 ዓመታት ብቻ ይቀረናል ብለዋል።
የዚህ ዓመቱ ጉባኤ ያንን ስምምነት እንደገና ለማየት፣ ለማሻሻል እና በአየርን ንብረት አጀንዳ ላይ እንደገና ለማሰብ ዕድል የሚሰጥ እንደሆነም ገልጸዋል።
በለሚ ታደሰ