ውክልና በሕግ ዓይን

6 Mons Ago
ውክልና በሕግ ዓይን

መቼም ሰው፣ ሰው ነውና በሁሉም ቦታ በሁሉም ሰዓት ለመገኘት ጊዜውም አቅሙም የለውም።

ከተፈጥሮ ሰው በተጨማሪም በሕግ መብት እና ግዴታ ያላቸው ተቋማትም በሰው ካልተወከሉ በስተቀር ግዑዝ ናቸውና ሕጋዊ ተግባራትን ለማከናወን አይችሉም።

ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሕፃናት እና በሕግ የተከለከሉ ሰዎች ደግሞ ሕጋዊ ተግባራትን ሚያከናውኑት በሞግዚታቸው በኩል ነው።

ከውል ወይም ከሕግ የሚመነጭ የውክልና ሥልጣን እና ሕጋዊ ውጤቶቹ በወካይ፣ በተወካይ እና በሦስተኛ ወገኖች ላይ የሚፈጥሯቸው መብት እና ግዴታዎች በተመለከተ መሠረታዊ ግንዛቤ እንዲኖረን የፍትሐ ብሔር ሕጋችን ስለወኪልነት ያስቀመጣቸውን ድንጋጌዎችን እንቃኛለን።

የፍ/ብ/ሕ/ቁ 2199 ውክልናን በመተርጎም ይጀምራል። “ውክልና ወካይ ለተወካዩ እንደራሴው ሆኖ አንድ ወይም ብዙ ሕጋዊ ሥራዎችን በወካዩ ስም ለማከናወን ግዴታ የሚገባበት ውል ነው” በሚል ይተረጉመዋል። ውክልና በግልጽ ወይም በዝምታ እንደሚሰጥ ሕጉ ቢፈቅድም የጽሑፍ ውክልና በሚያስፈልግባቸው ጉዳዮች ላይ ግን ውክልናው በጽሑፍ መሆን አለበት። ንብረትን ለማስተዳደር፣ ለመሸጥ፣ መለወጥ፣ በፍ/ቤት ቆሞ መከራከር እና ለመሳሰሉት ጉዳዮች የሚሰጡ ውክልናዎች በጽሑፍ መሆን አለባቸው።

ውክልና የሚፀናው ውክልናን ለማረጋገጥ እና ለመመዝገብ ሥልጣኑ በተሰጠው የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ ኤጀንሲ ወይም በክልል የፍትሕ ቢሮዎች ወይም ይህ ሥልጣን በሕግ በተሰጣቸው አካላት ፊት ተረጋግጦ ሲሰጥ እና ሲመዘገብ ነው።

በፍትሐ ብሔር ሕጋችን ላይ ሁለት የውክልና ዓይነቶች አሉ።

  1. ጠቅላላ ውክልና

ከሦስት ዓመት ለማያልፍ ጊዜ ንብረትን የማከራየት፣ ከብድር፣ ከሀብት የተገኘ ገቢን መሰብሰብ እና ማስቀመጥ፣ ለአከራዮች ደረሰኝ የመስጠት መሰል የአስተዳደር ሥራዎችን ብቻ እንዲያከናውን ለወኪሉ ሥልጣን የሚሰጥ ውክልና ነው። የንብረት ሽያጭ እና ባለቤትነትን ወደ ሦስተኛ ወገን የማስተላለፍ ሥልጣን ግን በዚህ  ዓይነቱ ውክልና  ውስጥ አይካተትም። ሆኖም ለሽያጭ የተመደቡ ዕቃዎችን ወይም ሰብሎችን መሸጥ ግን እንደ አስተዳደር ሥራ ስለሚቆጠር በጠቅላላ ውክልና ሥር ይመደባል።

  1. ልዩ ውክልና 

ይህ የውክልና ዓይነት ከአስተዳደር ሥራ ውጭ ያሉ ሌሎች ተግባራትን የረጅም ዘመን ኪራይን፣ የባንክ ገንዘብ ማውጣትን፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭን፣ ንብረትን ለብድር ዋስትና ማስያዝን፣ የለውጥ ውልን ከአንድ የአክስዮን ወይም የንግድ ማኅበር መግባትን እና ፍርድ ቤት ቆሞ መከራከርን ይመለከታል።

በተለምዶ ጠቅላላ ውክልና ተብሎ የሚጠራው ግን ሕጉ ከሚለው አንፃር ሲታይ የአስተዳደር ሥራ እና ልዩ ውክልናን ሥልጣኖችን ጭምር በአንድ ሰነድ ላይ በሰፊ ዝርዝር የሚያካትት ነው።

በሕጉ አገላለጽ ግን የንብረት ባለቤትነትን የማዛወር በወኪሉ ስም የመክሰስ/የመከሰስን እና መሰል የወካዩ መብት እና ግዴታ ላይ ዘላቂ ለውጥ ሊፈጥሩ የሚችሉ ሰፊ ሥልጣኖችን ለተወካዩ የሚሰጠው ግን ጠቅላላ ውክልና ሳይሆን ‘ልዩ ውክልና’ ነው። ልዩ ውክልና የተሰጠው ሰው ውክልናው ላይ የተጠቀሱትን ተግባራት እና ከተግባራቱ ባህሪ ጋር የሚያያዙ አስፈላጊ  ነገሮችን ማከናወን ይችላል። ለምሳሌ ንብረት የመሸጥ ውክልና የተሰጠው ሰው የሽያጩን ገንዘብ የመቀበል፣ ንብረቱን የማስረከብ እና ስመ ሀብቱን ለገዢው የማስተላለፍ ከሽያጭ ጋር የተያያዙ ተግባራትን የማከናወን ሥልጣንም አለው።

ወካዩ ለተወካዩ በሰጠው የሥልጣን ገደብ ስር ለሚሠራው ሥራ የሚገደድ ሲሆን ከውክልናው በላይ በቅን ልቦና የሠራውን ሥራም ወካይ በፍ/ብ/ሕ/ቁ በ2207 የማጽደቅ ግዴታ አለበት።

ተወካይ በሕጉ ላይ ጥብቅ የሆነ ቅን ልቦና እንዲኖረው የሚሠራውን ሥራ ሁሉ ለወካዩ ጥቅም እንጂ ለግሉ እንዳያደርግ ተደንግጓል።

ሕጉ ‘እንደ መልካም የቤተሰብ አባት’ ተገቢውን ትጋት እና ጥንቃቄ በማድረግ የውክልናውን ሥራ እንዲሠራ ተወካይ ላይ ግዴታ ጥሏል።

ወካዩ በውክልናው ላይ ከተሰጠው ሥልጣን በላይ ከሠራ ወኪሉ ላይ ለሚደርስ ጉዳት ተጠያቂነት አለበት። በተጨማሪም ከሥልጣኑ በላይ ወይም በሌለው ሥልጣን የተደረገ ውልም በወኪሉ ወይም መብት ባለው አካል ክስ ከቀረበበት ፍ/ቤት ሊሽረው ይችላል።

ውክልናውን ወካይ መስሎ በታየው ጊዜ የመሻር ሥልጣን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2226(1) ላይ የተሰጠው ሲሆን ወካይ የሞተ፣ በስፍራው ላይ ያለመኖሩ የተረጋገጠ፣ ሕጋዊ ተግባራትን ለመሥራት ችሎታ ካጣ ወይም ከከሰረ በፍ/ብ/ሕ/ግ 2230(1) መሠረት ውክልናው ይሻራል።

በነገራችን ላይ በውክልና ሊደረጉ እንደማይችሉ ሕጉ በግልፅ ካስቀመጣቸው ተግባራት አንዱ ኑዛዜ ማድረግ እና ጋብቻ መፈፀም ሲሆኑ የሚገርመው ጋብቻ መፈፀምን በተመለከተ በተሻሻለው የፌዴራሉ የቤተሰብ ሕጋችን ጋብቻን በውክልና መፈፀም እንደሚቻል ተፈቅዷል። ይህ ሊሆን የሚችለው ግን የፍትሕ ሚኒስትሩ በቂ ምክንያት መኖሩን አምነው ፍቃዳቸውን ሲሰጡ መሆኑ ተደንግጓል።

ለማንኛውም ውክልና ስንሰጥ ወይም ወኪል ስንሆን የውክልናውን አሰጣጥ በሕጉ አግባብ መሆኑን፣ ሕጋዊ ሥልጣኑ ባለው አካል ፊት ተረጋግጦ መመዝገቡን እና ሥልጣኑ ለሚፈለገው ተግባር ብቻ መሰጠቱን ማስተዋሉ ጠቃሚ ነው። ቸር እንሰንብት!


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top