የዓለማችን 7ቱ ምርጥ ስማርት ከተሞች

1 Yr Ago 2153
የዓለማችን 7ቱ ምርጥ ስማርት ከተሞች

በዓለም ላይ ያሉ ስማርት ከተሞች በስማርት ከተማነት ውጥናቸው ዘላቂ እና ኃይል ቆጣቢ ለመሆን እንዲሁም የካርበን ልቀትን ለመቀነስ ፈጠራ የታከለባቸው ስማርት ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ረገድ ትልቅ እመርታ አሳይተዋል።

በ2050 ከዓለም ሕዝብ 70% የሚሆነው በከተሞች እና በአካባቢው እንደሚኖር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተንብይዋል፤ ይህ ማለት የካርቦን ልቀት እና የኃይል ፍጆታ በየዓመቱ እየጨመረ ይሄዳል ማለት ነው።

በመሆኑም ስማርት የከተማ ትራንስፖርት አውታሮች፣ ለአካባቢ ተስማሚ የሆነ የውኃ አወጋገድ ሥርዓት እንዲሁም ከፍተኛ ኃይል የመቆጠብ ብቃት ያላቸው ሕንፃዎች አስፈላጊነት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ወሳኝ ናቸው። የስማርት ከተማ ፕሮግራሞች እና ውጥኖች እጅጉን አስፍላጊ የሚሆኑበት ደግሞ በዚህ ወቅት ነው።

ለመረጃ ልውውጥ ከሴንሰሮች ጋር ተሳስረው የተገጠሙ ዕቃዎችን (Internet of Things (IOT)) ጨምሮ በከተሞች ውስጥ ስማርት ቴክኖሎጂዎችን አንድ ላይ አጣምሮ አገልግሎት ላይ ማዋል የዜጎችን የኑሮ ጥራት ከማሻሻልም ባሻገር ለአጠቃላይ የሕዝብ ደኅንነት ወሳኝ ነገር ነው።

በዚህ ረገድ በ2020 የስማርት ከተማ ሰንጠረዥ የዓለም ስማርት ከተሞች በመሆን ሲንጋፖር፣ ሔልሲንኪ እና ዙሪክ ቀዳሚ ሆነዋል።

የአስተዳደር ልማት ኢንስቲትዩት ከሲንጋፖር የቴክኖሎጂ እና ዲዛይን ዩኒቨርሲቲ (SUTD) ጋር ባወጣው ዓመታዊ ሪፖርት፣ በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ መረጃ ላይ እንዲሁም ሰዎች ከተሞቻቸው ምን ያህል "ስማርት" እንደሆኑ ያላቸው ግንዛቤ ላይ በመመሥረት ለከተሞች ደረጃ ሰጥቷል።

ብዙ ዓለም አቀፍ ከተሞች በስማርት ቴክኖሎጂ ኢንቨስት ለማድረግ እንቅስቃሴውን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ፤ ከዚህ አንፃር በዘመናዊ ከተማ ፕሮጀክቶቻቸው የመሪነቱን ስፍራ የያዙ ሰባት ስማርት ከተሞች የሚከተሉት ናቸው።

1ኛ. ሲንጋፖር

የስማርት ከተሞችን ጉዳይ ስንመለከት ከአብዛኞቹ ዝርዝሮች ውስጥ ብዙውን ጊዜ ቀዳሚዋ ሲንጋፖር ናት።

ሲንጋፖር በ2014 “ስማርት ኔሽን” ውጥንን ከጀመረች በኋላ፣ በመንግሥት እና በግሉ ሴክተሮቿ መጠነ-ሰፊ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን አስተዋውቃለች።

የሕዝብ ማመላለሻ ለሚጠቀሙ 7.5 ሚሊዮን መንገደኞች ያለችግር እንዲንቀሳቀሱ እና ክፍያዎችን እንዲፈፅሙ ንክኪ አልባ የክፍያ ቴክኖሎጂ በስፋት ሥራ ላይ ውሏል።

የአረጋውያን ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ የዲጂታል የጤና ሥርዓት ተዘርግቷል። ለዚህም በተመሳሳይ ጊዜ በቪዲዮ የሚደረግ የጤና ምክርን መደበኛ ማድረግ እንዲሁም ታማሚዎችን ለመከታተል ተለባሽ የበይነ-መረብ መሣሪያዎች አገልግሎት ላይ ውለዋል።

ከዚህም ባሻገር፣ ሲንጋፖር ከተሽከርካሪ ሙሉ በሙሉ የፀዳ አዲስ ኢኮ-ስማርት ከተማ ዕቅዷን በ2021 ይፋ አድርጋለች።

በሲንጋፖር ምዕራባዊ ክልል ቴንጋህ በተባለ አካባቢ ውስጥ ለመገንባት የታቀደው የጫካ ከተማ 42 ሺህ ቤቶች ያሏቸው አምስት የመኖሪያ ወረዳዎች እንዲሁም ለእግረኞች እና ለብስክሌት ጋላቢዎች ደኅንነታቸው የተጠበቀ ስፍራዎች ይኖሩታል።

2ኛ. ሔልሲንኪ፣ ፊንላንድ

ሔልሲንኪ እ.አ.አ. በ2035 ከካርቦን ነፃ የመሆን ዓላማ አውጥታ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን ግቡ ላይ ለመድረስም በጥሩ ጉዞ ላይ መሆኗ እየተነገረ ነው።

ከተማዋ በያዘችው ዘመቻ በ1990 ከነበረው የካርቦርን ልቀት መጠን በ2017 በ27 በመቶ መቀነስ መቻሏ ነው የተለገጸው።

የሔልሲንኪ ሌላኛው ግብ በትራፊክ ምክንያት የሚለቀቀውን የካርቦን መጠን እ.አ.አ በ2035 በ69 በመቶ መቀነስ ሲሆን ይህንን ለማሳካትም የከተማ አውቶቡሶችን ሙሉ በሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ መቀየር፣ የሜትሮ እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎችን የማስፋፋት እርምጃዎችን እየወሰደች ትገኛለች።

በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈጠረው ሙቀት በሔልሲንኪ ከሚፈጠረው የካርቦን ልቀቶች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሸፍን በመሆኑ ከተማዋ በእድሳት ወቅት የኃይል ቆጣቢ እርምጃዎችን በመተግበር ላይ አተኩራለች።

ይህም ከሕንፃዎች የሚወጣውን ልቀት በ80 መቀነስ እና በከተማው ሕንፃዎች ውስጥ የበለጠ ታዳሽ የኃይል አጠቃቀምን ያካትታል።

3ኛ. ዙሪክ፣ ስዊዘርላንድ

በዙሪክ የስማርት ከተማ ሂደት የተጀመረው በመንገድ መብራት ፕሮጀክት ነው። ሴንሰሮችን ተጠቅመው ከተማዋ ከትራፊክ ፍሰት ጋር የሚጣጣሙ የመንገድ መብራቶችን አስተዋውቀዋል፤ የመንገድ መብራቶቹ የትራፊክ ፍሰቱን ሁኔታ በመከተል ብርሃን የሚጨምሩ ወይም ብርሃናቸውን የሚቀንሱ ናቸው። ይህ ፕሮጀክት እስከ 70 በመቶ ኃይል መቆጠብ አስችሏል።

ይህንን ስማርት የመንገድ መብራት ፕሮጀክትን በመላ ከተማዋ ያዳረሰች ሲሆን አካባቢያዊ መረጃን የሚሰበስቡ፣ የትራፊክ ፍሰቱን የሚለኩ እና እንደ የሕዝብ የዋይ-ፋይ አንቴና የሚያገለግሉ የሴንሰር ቴክኖሎጂዎችን ዘርግታለች።

የከተማውን ማሞቂያ፣ ኤሌክትሪክ እና ማቀዝቀዣ የሚያገናኘው የስማርት ሕንፃ አስተዳደር ሥርዓትም ከፍተኛ ውጤታማነት የታየበት መሆኑ ነው  የተነገረው።

4ኛ. ኦስሎ፣ ኖርዌይ

የኖርዌይዋ ዋና ከተማ ሙሉ ለሙሉ ወደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እየገባች ሲሆን እ.አ.አ በ2025 ደግሞ በጠቅላላው ከተማ ውስጥ ያሉ ሁሉም ተሽከርካሪዎች ወደ ኤሌክትሪክ እንዲገቡ ዕቅድ አውጥታለች። ይህም 670 ሺህ የሚጠጉ ዜጎቿን ግምት ውስጥ ስናስገባ አስደናቂ ውጤት ይኖረዋል።

ዜሮ የካርቦን ልቀት ሥርዓትን ለሚከተሉ ተሽከርካሪዎች ከወዲሁ ማበረታቻዎች ተዘጋጅተዋል፤ ከእነዚህም መካከል ነፃ የመኪና ማቆሚያ፣ የአውቶቡስ መስመሮችን መጠቀም እንዲሁም ዝቅተኛ የግብር እና የአገልግሎት ክፍያ ተመን ናቸው።

እ.አ.አ. በ2050 ከተማዋ ከካርቦን ነፃ ለመሆን አቅዳለች፤ ለዚህም በኦስሎ የዜሮ-ልቀት የግንባታ ቦታዎችን እና ነባር ሕንፃዎችን ክብ የቆሻሻ አያያዝ እና የአረንጓዴ ኢነርጂ ሥርዓቶችን በማዘጋጀት በጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች።

5ኛ. አምስተርዳም፣ ኔዘርላንድስ

የአምስተርዳም ስማርት ከተማ ፕሮጀክት በ2009 የጀመረ ሲሆን በከተማው ውስጥ ከ170 በላይ የተለያዩ ሥራዎችን ያካተተ ነው።

በተለይ በአምስተርዳም ጎልቶ የሚጠቀሰው ፈጠራ የታከለበት ሥራዎችን የመሥራት ችሎታዋ ነው፤ ከእነዚህም ለቆሻሻ ማንሻነት ለሚያገለግሉ የኤሌክትሪክ መኪናዎች ታዳሽ ኃይል መጠቀም፣ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ ፌርማታዎችን፣ ማስታወቂያ ሰሌዳዎችን እና መብራቶችን መትከሏ እንዲሁም የሰዎችን አንድ ቦታ ላይ መታጨቅን ለመቅረፍ ተንሳፋፊ መንደሮችን መገንባት እና ለመሬት ባለቤትነት ጥያቄ ሌላ አማራጭ መፍጠሯ የሚጠቀሱ ናቸው።

በከተማው ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ በሥራ ላይ ያሉ የንግድ እና የግል ቤቶች በኃይል ቆጣቢ ጣሪያዎች የተሸፈኑ ናቸው፤ እነዚህ ጣሪያዎች አውቶማቲክ የመብራት መቀየሪያዎች፣ ስማርት ሜትሮች እና እጅግ ዝቅተኛ ኃይል የሚጠቀሙ LED መብራቶች የተገጠሙላቸው ናቸው።

6ኛ. ኒው ዮርክ፣ አሜሪካ

በመቶዎች የሚቆጠሩ ስማርት ሴንሰሮች እና ቴክኖሎጂዎች ሙከራ ተደርጎባቸው በተለያዩ የኒው ዮርክ ከተማ አውራጃዎች ተተክለዋል። ይህም ከተማዋ የነደፈችው የ2020 የስማርት ከተማ የሙከራ መርሐ-ግብር አካል እንደሆነ ይጠቀሳል።

መርሐ-ግብሩ እንደ ቆሻሻ አያያዝ እና አሰባሰብ ያሉ አገልግሎቶችን በተሻለ መንገድ ለማስተዳደር እንዲረዳ መረጃ ይሰበስባል።

ኒው ዮርክ ከፍተኛ የዋይ-ፋይ አቅም ያላቸው እንዲሁም ስልኮች በኦንላይን ቻርጅ የሚደረጉበት ጣቢያን ያካተተ የንክኪ አልባ ቴክኖሎጂዎች ስማርት ማዕከሎችንም እያስተዋወቅ ነው።

ኒው ዮርክ ከተማ ፈጠራዎችን ለማበረታታት የከተማዋን ክፍት የመረጃ ስብስቦች በተሻለ ሁኔታ የሚጠቀሙ መተግበሪያዎችን ለሚፈጥሩ ሰዎች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት የሚያስገኝ ዓመታዊ ውድድር ታካሂዳለች።

7ኛ. ሴዑል፣ ደቡብ ኮሪያ

በዓለም የመጀመሪያዋ ስማርት ከተማ በመባል የምትታወቀው ‘ሶንግዶ’ መገኛ የሆነችው ሴዑል፣ የስማርት ቴክኖሎጂ ዘመቻዋን ከጀመረችበት ከ2014 (እ.አ.አ) ጀምሮ ግስጋሴዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ነው የሄደው።

መረጃ የሴዑል የስማርት ከተማ ፕሮጀክቶች ዋነኛ መሠረት ነው፤ በሴንሰሮች እና በከተማው ውስጥ በተዘረጉ CCTVዎች የሚለኩ እንደ የትራፊክ ፍሰት፣ የፍጥነት እና የአየር ጥራት ያሉ የከተማ ሁኔታዎችን መረጃ ተሰብስበው ይተነተናሉ፤ የትንታኔው ውጤትም ለስማርት መሠረተ-ልማት እና አገልግሎቶች ጠንካራ መሠረት ይሆናል።

ይህም ቴክኖሎጂው በዕድሜ በገፉ ሰዎች ላይ እንዲያተኩር በማድረግ በከተማዋ ለብቻቸው የሚኖሩ አረጋዊያንን ለመርዳት የተጀመረ የደኅንነት ኢንሼቲቭ እንደሆነ ይነገራል።

በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ካልታየ ወይም ያልተለመደ የሙቀት መጠን፣ እርጥበት ወይም መብረቅ በአካባቢ ሴንሰሮች ከተደረሰበት የሚመለከታቸው ሠራተኞች እና የድንገተኛ አደጋ አገልግሎት ባለሙያዎች ወዲያውኑ ጉዳዩን እንዲያጣሩ ይደረጋል።

በተጨማሪም በከተማዋ ሊከሰቱ የሚችሉ የወንጀል ድርጊቶችን የሚጠቁም አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ (AI) መርማሪ በመፍጠር ልትጠቀምበት እያሰበች ነው።

ሴዑል የ5ጂ ቴክኖሎጂን በተንቀሳቃሽነት እና በመጓጓዣ ከተጠቀሙባቸው የመጀመሪያዎቹ ከተሞች መካከል አንዷ ሆናለች። 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top