ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች የሚገኘው የወርቅ ምርት ቀንሷል - የማዕድን ሚኒስቴር

8 Mons Ago
ከባህላዊ ወርቅ አምራቾች የሚገኘው የወርቅ ምርት ቀንሷል - የማዕድን ሚኒስቴር

የማዕድን ሚኒስቴር የ2016 በጀት አመት እቅድ እና የመጀመሪያ ሩብ አመት አፈጻጸሙን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቧል፡፡

በዚሁ ወቅት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ የሰጡት የማዕድን ሚኒስትሩ ኢንጅነር ሀብታሙ ተገኝ፤ በመጀመሪያው ሩብ አመት በወርቅ ምርት በባህላዊ እና በኩባንያ ደረጃ የወርቅ ማምረት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይም ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ክልል በባህላዊ ወርቅ አምራቾች ከፍተኛ ውጤት ይመዘገብ እነደነበር ገልጸው፤ በሩብ አመቱ ግን ማሽቆልቆሉን ተናግረዋል፡፡

በሩብ አመቱ በኩባንያ ደረጃ ያለው የወርቅ ምርት አፈጻጸም 78 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው፤ በባህላዊ የወርቅ ምርት ያለው አፈጻጸም ግን ወደ 22 በመቶ መውረዱን ገልጸዋል።

በሩብ ዓመቱ ከወርቅ ምርት 112 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 63 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

ባለፉት ጊዜያት በሀገሪቷ በነበሩ ባህላዊ ወርቅ አምራቾች ይመሩቱ የነበሩ የወርቅ ምርቶች ትልቁን ድርሻ ይይዙ ነበር ያሉት ሚንስትሩ፤ ባለፈው ሩብ አመት የነበረው የምርት መጠን መቀነሱን እና አጥጋቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።

በሀገሪቷ በአንዳንድ አካባቢዎች ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት የወርቅ ምርት መቀነሱን ጠቅሰው፤ ይህም ለአፈጻጸሙ መቀነስ አስተዋጽዖ እንዳለው ገልጸዋል።

ለዚህም በሚቀጥሉት ጊዜያት የተለያዩ ማሻሻያዎች እና ሪፎርሞች እንደሚደረግ ነው ሚኒስትሩ የገለፁት።

በተስሊም ሙሀመድ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top