ሁሉም የአማራ ክልል አመራሮች የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር አብዱ ሁሴን አሳሰቡ።
በክልሉ ወቅታዊ ሁኔታዎች እና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ ውይይት በደሴ እና በደብረ ብርሃን ከተሞች እየተካሄደ ነው።
በደሴ ከተማ በተካሄደው ውይይት ላይ የተገኙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለፁት፤ የጥፋት ሀይሎች ክልሉን በሀይል በማፍረስ ስልጣን ለመቆናጠጥ ያደረጉትን ጥረት በቅንጅት ማክሸፍ ተችሏል።
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሕግ ለማስከበር በተደረገው ጥረት ሰላሙ በመሻሻሉ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወደ መደበኛ ስራቸው እየተመለሱ ቢሆንም፤ በአንዳንድ አካባቢዎች በጫካ መሽገው መንገድ በመዝጋትና በመዝረፍ ህብረተሰቡን የሚያንገላቱትን ሁሉም ሊታገላቸው እንደሚገባ ገልጸዋል።
አመራሩ ህብረተሰቡን በየደረጃው አደራጅቶ ሰላሙን ከመጠበቅ ባሻገር የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎችን በአግባቡ በመመለስ የመሪነት ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የወረኢሉ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደለለ ቸርነት በበኩላቸው፤ ህብረተሰቡን በየሰፈሩና ቀጣናው በማደራጀት የአካባቢውን ሰላም በራሱ እንዲጠብቅ ውይይቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
ለዚህም የጸጥታ መዋቅሩን ከህብረተሰቡ ጋር አቀናጅቶ ህግ እንዲከበር ከማድረግ ባለፈ “የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄ ለመመለስ ቁርጠኛና ዝግጁ ነን” ብለዋል፡፡
በመድረኩ የደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎና ዋግ ኽምራ ብሄረሰብ ዞኖች እንዲሁም የደሴ፣ የወልድያና የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር አመራር አባላትና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።
በተመሳሳይ ዜና በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተሞች ልማት ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር አህመዲን መሐመድ በደብረ ብርሃን በተካሄደ ውይይት ላይ እንደገለፁት፤ አመራሩ የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በመፍታት የመሪነት ሚናውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
በሰላም፣ በልማትና በዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ረገድ ህብረተሰቡን በማወያየትና በቅንነት በማገልግል ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚጠቅበትም አስገንዝበዋል።
አሁን ላይ በክልሉ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ በማድረግ የኑሮ ውድነትና የስራ አጥነት ችግሮችን ከመፍታት ባሻገር አመራሩ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ ስራዎችን በቁርጠኝነት እንዲሰራም ማሳሰባቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
በሰሜን ሸዋ ዞን የቡልጋ ከተማ አስተዳደር አመራር አባል ወይዘሪት ዮዲት በቀለ እንደገለፁት፤ በክልሉ የሰላም፣ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱ ህብረተሰቡን በማስተባበር ለመስራት ተዘጋጅተዋል።
በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ጅሌ ጥሙጋ ወረዳ አመራር አቶ መሐመድ አህመድ በበኩላቸው፤ አሁን ላይ ህዝቡ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ከመጠየቅ ባለፈ የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች እንዲፈቱለት እያነሳው ለሚገኘው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰሩም ገልፀዋል።
የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር አመራር ወይዘሮ እጥፍወርቅ ደጀኔ በበኩላቸው፤ ባገኙት ስልጠና ህብረተሰቡን በቅንነት በማገልገል የተሳሳቱ ትርክቶች እንዲስተካከሉ የማድረግ ሚናቸውን እንደሚወጡም አስታውቀዋል።