በዶሃ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን የኢትዮጵያ ተሳትፎ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ መሆኑ ተገለፀ

1 Yr Ago 1909
በዶሃ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን የኢትዮጵያ ተሳትፎ የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ መሆኑ ተገለፀ

“ኤክስፖ 2023 ዶሃ” ዓውደ ርዕይ የሆርቲካልቸር ዘርፍን ለማሳደግ ያለመና በሁለት ዓመት አንዴ የሚካሄድ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ሲሆን፤ ከግሉ ኩባንያዎች በተጨማሪ 80 የሚጠጉ አገራት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ።

ከሶስት ሚሊዮን በላይ ጎብኝዎች ትኩረት ይስባል ተብሎ ይጠበቃል:: ዓላማውም በግብርናው ዘርፍ ዘላቂ ፈጠራዎችን ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ እና በረሃማነትን ለመዋጋት ነው።

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመካከለኛው ምሥራቅ 'አረንጓዴ በረሃ፣ የተሻለ አካባቢ' በሚል መሪ ቃል በዶሃ በተከፈተው እና ለ179 ቀናት በሚቆየው “ኤክስፖ 2023 ዶሃ” ዓለም አቀፍ የአበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ዓውደ ርዕይ ላይ እየተሳተፈች መሆኑ ይታወቃል።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የግብርና ሚኒስቴር፣ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ የአበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራቾች ማህበር እና መሰረታቸውን በዶሃ ያደረጉ በግብርና ውጤቶች ንግድ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች ከኤምባሲው ጋር በመተባበር ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅምና ምቹ ሁኔታዎችን በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ።  

መድረኩ ኢትዮጵያ በኳታር የተፈጥሮ ሃብቷን፣ በታሪክ እና በአርኪኦሎጂያዊ ቅርሶች የተሞላው ባህሏን እና እሴቶቿን በማስተዋወቅ የሕዝብ ለሕዝብ ወዳጅነት ማጠናከር፣ የአገሪቱን ገጽታ መገንባት ብሎም በአበባ አትክልት እና ፍራፍሬ ዘርፍ እምቅ አቅሟን ለማሳየት ያስቻለ መሆኑን በቀጠር፣ በኢራን እና በየመን ኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ፈይሰል አሊይ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ስላሉ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እና አማራጮች በመስኩ ስላሉ የማበረታቻ ማዕቀፎች እና ዕድሎች እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ኩባንያዎች በአገሪቷ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያደርገውን ድጋፍ ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ዕድል የፈጠረ ኤግዚብሽን ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

በኳታር ዶሃ እየተካሄደ የሚገኘው ዓለም አቀፍ ሆርቲካልቸራል ኤክስፖ 2023 አካል በሆነው እና ለአምስት ቀናት የሚቆየው፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ65 ሀገራት በተሰባሰቡ ከ300 በላይ ሰዓሊያን የተካተቱበት የስዕል እና ፋሽን ዓውደ ርዕይ ላይ ኢትዮጵያውያን ሰዓሊዎች ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

በዓውደ ርዕዩ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ በኳታር ፣ በኢራን እና በየመን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ፈይሰል አሊይ ፣ ፕሮፌሰር ኻሊድ ኢብራሂም አል-ሱለይቲ የካታራ መንደር ዋና ስራ አስኪያጅ፣ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ አባላት እንዲሁም ሌሎች የተለያዩ አገራት አምባሳደሮች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ተከፍቷል።

በዓውደ ርዕዩ ላይ የፈጠራ ሥራቸውን ያቀረቡት አምስት ኢትዮጵያውያኖች ሲሆኑ፤ የስዕል ዓውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት፣ የሰው ልጅ መገኛ መሆኗን መልከዓ ምድርና የሆልቲካልቸው እምቅ ሀብት ለታዳሚው በማሳየት የሀገራችንን ገፅታ የገነባ ነው፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top