የመደመር እሳቤ ለትውልድ ግንባታና ለአገር ዘላቂ እድገት የሚጠቅሙ ጥልቅ ምልከታዎችን የያዘ ነው- በፓኪስታን የፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ

248 Days Ago
የመደመር እሳቤ ለትውልድ ግንባታና ለአገር ዘላቂ እድገት የሚጠቅሙ ጥልቅ ምልከታዎችን የያዘ ነው- በፓኪስታን የፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ
የመደመር እሳቤ ለትውልድ ግንባታና ለአገር ዘላቂ እድገት ጠቃሚ የሆኑ ጥልቅ ምልከታዎችን የያዘ መሆኑን በፓኪስታን የፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ ዋሲም አጅማል ቻውድሪ ገለጹ።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ ኢምባሲ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጻፈውን "የመደመር ትውልድ" መጽሃፍ የማስተዋወቂያ መርሃ ግብር አካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የፓርላማ ተወካዮች፣ ፖለቲከኞች፣ የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ፣ መገናኛ ብዙሃንና ሲቪል ሶሳይቲ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በፓኪስታን የፌዴራል ትምህርት ሚኒስቴር ዋና ጸሐፊ ዋሲም አጅማል ቻውድሪ፤ የመደመር ጽንሰ ሀሳብ አንድነትን ማጠንከርና ትውልድን ለማነጽ የሚያስችሉ ምክረ ሀሳቦች የተካተቱበት መሆኑን ገልጸዋል።
የመደመር ትውልድ መጽሃፍ የሰው ልጅን የህይወት ቁርኝት በጥልቅ እይታና ሰፊ ማብራሪያ የያዘ መሆኑን ተናግረዋል።
መደመር ከሀገር የተሻገረ እሳቤን በመያዝ አንድነትን፣ ትብብርና አብሮነትን የሚያጸና ጥልቅ የሆኑ እይታና ቁምነገሮችን የያዘ መሆኑንም አንስተዋል።
በመሆኑም የመደመር እሳቤን መሰረት በማድረግ የትውልድ ግንባታን በማጠናከር አገርን በፅኑ መሰረት ላይ ማኖር ይገባል ነው ያሉት።
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር፤ የመደመር እሳቤ የተሻለ እና ጠንካራ ትውልድ ለመገንባት እንዲሁም ያለፈውን፣ አሁን ያለውንና መጪውን ለማስተሳሰር ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በአገር ግንባታ ሂደት በመደመር እና በጥምረት መሥራት ያለውን ፋይዳ በስፋት የተብራራበት መሆኑን ገልጸዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አመራር ሰጪነት ተግባራዊ የተደረገው የአረንጓዴ ልማት የአመራር ስኬታቸውን ያመላከተ መሆኑን በመድረኩ አንስተዋል።
አፍሪካ እየተለወጠ ባለው የዓለም ፖለቲካ ውስጥ ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንድትሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽኑ አቋም ይዘው እንደሚሰሩ ጠቅሰው አፍሪካዊያን በአህጉራዊ አጀንዳዎች ላይ በጋራ እየሰሩ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የአፍሪካና ፓኪስታን ህብረት ፕሬዝዳንት ዛፋር ባክታዋሪ፤ የመደመር እሳቤ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለፓኪስታንም ጠቃሚ ምክረ ሀሳብ ያለው መሆኑን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top