ኢትዮጵያ አዲስ እየተዋወቀ ላለው የሥነ-ፈለክ ቱሪዝም ተመራጭ የሆኑ ቦታዎች ያሏት ሀገር ናት:- ዓለም አቀፉ የሥነ-ፈለክ ህብረት

7 Mons Ago
ኢትዮጵያ አዲስ እየተዋወቀ ላለው የሥነ-ፈለክ ቱሪዝም ተመራጭ የሆኑ ቦታዎች ያሏት ሀገር ናት:- ዓለም አቀፉ የሥነ-ፈለክ ህብረት

ዓለም አቀፉ የሥነ-ፈለክ ሕብረት ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 386ኛው አውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

"የሥነ-ፈለክ ቱሪዝምን ለማሳደግ የሰማይ እና የሥነ-ፈለክ ቅርሶች ሚና" በሚል እየተካሄደ ያለው አውደ ጥናቱ የሥነ-ፈለክ ቅርሶችን በመጠበቅ ለሰው ልጆች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ለማዋል ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ምክረ ሃሳቦችን ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ፒ ኤች ዲ) የኢትዮጵያ መንግስት ከህዋ ሳይንስ ልማት ተጠቃሚ ለመሆን ከተቋም ምስረታ እስከ ሥነ-ፈለክ ሳይንስ ፖሊሲ ቀረፃ የደረሱ እርምጃዎችን መውሰዱን ተናግረዋል።

ከሥነ-ፈለክ ቱሪዝም ተጠቃሚ ለመሆን የሰማይ (ጥቁር ሰማይ) እና የሥነ-ፈለክ ቅርሶች ጥበቃ ላይ ዓለም በትብብር መስራት ይኖርበታል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ካልተነካው የሥነ-ፈለክ ቱሪዝም ተጠቃሚ ለመሆን እንሰራለን ብለዋል።

የዓለም አቀፉ የሥነ-ፈለክ ህብረት ምክትል ሊቀመንበር ሰለሞን በላይ (ፒ ኤች ዲ) ህብረቱ በኮሙኒኬሽን፣ በትምህርትና በሥነ-ፈለክ ቦታዎች ጥበቃ በትኩረት እንደሚሰራና ሀገራት ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት ያደነቁት ምክትል ሊቀመንበሩ ሀገራት ትብብራቸውን ማጠናከር እንዳለባቸውም አጽንዖት ሰጥተዋል።

አውደ ጥናቱ የሥነ-ፈለክ ቱሪዝምን ለማሳደግ እና ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን ጥቁር ሰማይን የሚጎዱ ሰው ሰራሽ መብራቶችን መፍትሄ መስጠት፣ ዘርፉን ለህዝብ ማስተዋወቅ፣ ለሥነ-ፈለክ ቱሪዝም መዳረሻ የሆኑ ቦታዎችን መለየትና ማስመዝገብ፣ ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በሚሉ እና ሌሎችም ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው።

አስትሮ ቱሪዝም በልዩ የሰማይ ባህርያቸው የሚታወቁ መዳረሻዎችን መጎብኘት ላይ የሚያተኩር  ሲሆን በሰማይ ላይ ያሉ ከዋክብቶችን፣ ፕላኔቶችን፣ ጋላክሲዎችን እና ሌሎች የሥነ-ፈለክ ቅርሶችን ለማየት በሚመቹ ቦታዎች ላይ የሚደረግ ጉብኝትን ወይንም እይታን የሚመለከት ስለመሆኑ ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top