በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እየተገነቡ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች የረጅም ጊዜ ጥያቄዎቻችንን የመለሱ ናቸው

3 Mons Ago
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እየተገነቡ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች የረጅም ጊዜ ጥያቄዎቻችንን የመለሱ ናቸው
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እየተገነቡ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች የረጅም ጊዜ ጥያቄዎቻንን የመለሱ ናቸው ሲሉ የሆሳዕና ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።
 
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እየተገነቡ ከሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል በሀዲያ ዞን የሆሳዕና-ጃጁራ-ጊንቢቹ-ጃቾ 49 ነጥብ 25 ኪሎ ሜትር አስፋልት ኮንክሪት መንገድ ይገኝበታል።
 
በተጨማሪም የሆሳዕና ከተማን ከተለያዩ አጎራባች ከተሞች ጋር የሚያገናኝ 5 ነጥብ 13 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ እየተገነባ ሲሆን ፕሮጀክቱ በቀጣይ ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።
 
በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሶዶ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ጽኅፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ ተመስገን አሸናፊ መንገዶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
 
የሆሳዕና ከተማን ከተለያዩ አጎራባች ከተሞች ጋር የሚያገናኘው መንገድ በከተማው ላይ የሚፈጠረውን የትራፊክ መጨናነቅ በጉልህ የሚቀንስ መሆኑን ገልጸዋል።
 
የሆሳዕና-ጃጁራ-ጊንቢቹ-ጃቾ 49 ነጥብ 25 ኪሎ ሜትር አስፋልት መንገድም በርካታ ነዋሪዎች ያሉባቸውን ወረዳዎች ከማዕከል ጋር የሚያገናኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
 
መንገዱ በዞን ከተማ 22 ሜትር፣ በወረዳ ከተማዎች 20 ሜትር፣ በቀበሌ ከተማዎች 15 ሜትር እንዲሁም በገጠር ከ8 እስከ 10 ሜትር ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ የሚገነባ መሆኑንም ተናግረዋል።
 
መንገዱን በሶስት ዓመት ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ግንባታው የአፈር ቆረጣ እና ሙሌት፣ የሰብ ቤዝ እና ቤዝ ኮርስ፣ አስፋልት ንጣፍ፣ ድልድይ፣ የከልቨርቶች እንዲሁም የአነስተኛ፣ መካከለኛና የከፍተኛ ውኃ መፋሰሻ ቱቦዎች ግንባታ ሥራዎችን ያካትታል ብለዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሆሳዕና ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እየተገነቡ ያሉ የመንገድ ፕሮጀክቶች የረጅም ጊዜ ጥያቄዎቻችንን የመለሱ ናቸው ብለዋል።
 
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ግርማ ሳይሞ የሆሳዕና-ጃጁራ-ጊንቢቹ-ጃቾ መንገድ ከ10 ዓመት በፊት ይሰራል ተብሎ የነበረ መሆኑን አስታውሰው መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት መንገዱን በመጀመሩ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጭ አቶ ታምራት ጥሌ መንገዱ ለብዙ ጊዜ በጉጉት ስንጠብቀው የነበረ ነው ብለዋል።
 
መንገዱ ከዚህ ቀደም የነበረውን እንግልት የሚቀንስና የግብርና ውጤቶችን በቀላሉ ወደ ገበያ ለማድረስ እንደሚረዳ ተናግረዋል።
 
አቶ ታሪኩ ኤርጎጎም በከተማው ከዚህ ቀደም የነበረው መንግድ ጠባብ እንደነበረና በዚህ መጠን መገንባቱ ለመንገዱ የትራፊክ እንቅስቃሴ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ነው ያስረዱት።
 
የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም የመንገዶቹ መገንባት በተለይም ለአካባቢው ነዋሪዎች ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
 
የሃዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ መንገዶቹ ዋና ከተማውን ከወረዳዎች፣ ከአጎራባች ዞኖችና ከተማዎች ጋር በማሰተሳሰር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
 
ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ በሥፍራው በስፋት የሚገኙትን የተለያዩ የፍራፍሬ፣ የቡና፣ ድንች፣ ገብስ፣ ባቄላ ምርቶች ወደ ማዕከላዊ ገበያ በቀላሉ ማድረስ ያስችላል ብለዋል።
በመሆኑም ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
 
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር ደበበ ገብሬ በበኩላቸው መንገድ ከከተማ እድገት ጋር የሚያያዝ መሆኑን ገለጸዋል።
 
ፕሮጀክቶቹ በአካባቢው የሚመረቱ ምርቶችን በፍጥነት ወደ ገበያ ከማቅረብ ባሻገር በዞኑ የሚገኙትን የሰንቆ ተራራና ጠሌ ትክል ድንጋይን የመሳሰሉ የቱሪስት መዳረሻዎች ለጎብኚዎች ምቹ በማድረግ በኩል የጎላ ሚና እንደሚጫወቱም ነው የተናገሩት።

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top