ዓለማችን በዕለቱ

1 Yr Ago 5319
ዓለማችን በዕለቱ

አፍሪካ

ንጉስ ቻርለስ ሶስተኛ ኬንያውያን የነጻነት ትግል ላይ በነበሩበት ወቅት የተፈፀመባቸው አጸያፊ እና ፍትሃዊ ያልሆነ የሃይል እርምጃ አግባብ አለመሆኑን አመኑ።ንጉሱ በናይሮቢ በተካሄደው የመንግስት ግብዣ ላይ ባደረጉት ንግግር በተፈጠረው የታሪክ ስህተት ሀዘናቸው ትልቅ መሆኑን እና መፀፀታቸውን ገልጸው የምናድበሰብሰው ጉዳይ አይደለም ብለዋል። 

ነገር ግን ንጉሱ በመንግስት ሚኒስትሮች የተፈረመ መደበኛ የይቅርታ ጥያቄ አላቀረቡም።የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በሰጡት ምላሽ ንጉሱ ይቅርታ መጠየቃቸውን አወድሰዋል።

 

እስያ

200 የሚጠጉ የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች ግብፅን ከጋዛ ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ በሚገኘው ራፋህ ማቋረጫ በኩል ወደ ጋዛ ሰርጥ መግባታቸውን የፍልስጤም ባለስልጣን ተናገሩ።በአጠቃላይ 39 የእርዳታ ቁሶችን የጫኑ መኪኖች በራፋህ  በኩል ወደ ጋዛ መግባታቸውን ተናግረዋል ሲል የፍልስጤም ባለስልጣንን ጠቅሶ አል ሀዳዝ የቴሌቪዥን ጣቢያ  ዘግቧል።እንደ ቱርክ ቀይ ጨረቃ ማህበር ሪፖርት በጋዛ ያለውን የሰብዓዊ እርዳታ ጥያቄ ለመመለስ  በየቀኑ ቢያንስ 100 እርዳታ የጫኑ መኪኖች መግባት አለባቸው።

 

ደቡብ አሜሪካ

ከስድስት ቀናት በፊት በሜክሲኮ አካፑልኮ ሪዞርት አካባቢ ላይ ጉዳት ባደረሰው  ኦቲስ የተሰኘ አውሎ ነፋስ ምክንያት በርካታ ሰዎች እስካሁን ደብዛቸው መጥፋቱን የአካባቢው አስተዳደር አስታወቀ።በአደጋው እስካሁን 45 የአካባቢው ነዋሪዎች ህይወታቸው አልፏል።

መንግስት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችን ለማገዝ ወታደሮችን እና ፖሊሶችን ወደ አካባቢዋ የላከ ሲሆን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አንድሬስ ማኑዌል ሎፔዝ  አካፑልኮን በፍጥነት መልሰው ለማቁቋም ቃል ገብተዋል።

 

አውሮፓ

የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ  5.3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የንግድ ገደብ ይጥላል ተብሎ ይጠበቃል ሲል ብሉምበርግ ዘግቧል።እንደ ብሉምበርግ ምንጮች ከሆነ፣ በቅርቡ ይጣላሉ ተብለው የሚጠበቁት ማዕቀቦች ሩሲያ ኤክስፖርት በምታደርጋቸው የኬሚካል ምርቶች እና ሌሎች ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች ላይ ተጽእኖ ይኖራቸዋል።  ከዚህ ባለፈ ህብረቱ አሉሚኒየም እና የግንባታ እቃዎች እንዲሁም የመጓጓዣ ምርቶች እና የከበሩ ድንጋዮች ወደ አባል ሀገራት እንዳይገቡ ሊያደርግ ይችላል ተብሏል።የአውሮፓ ህብረት ማዕቀብ ዝርዝር ከ100 በላይ ግለሰቦች እና 40 የንግድ ተቋማትንም ያካትታል ተብሎ ይጠበቃል። 

 

ሰሜን አሜሪካ

የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን ሩሲያ ወደፊት ኔቶን ልትገዳደር ትችላለች ሲሉ ተናገሩ።ሚንስትሩ ይዋል ይደር እንጂ  ፑቲን ኔቶን እንደሚፈታተኑ ምንም ጥያቄ የለውም፣ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገው ወታደራዊ ዘመቻ ከተሳካ የጎረቤት ሀገራትን በተለይም የባልቲክ ሀገራትን ደህንነት አደጋ ላይ ይጥላል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top