ብዙ ጊዜ አንድ ሰው የስኳር ህመም አለበት ሲባል እንሰማለን ይህ የስኳር በሽታ ምንድን ነው? መንስኤውስ ? የሚለውን በዛሬው የጤና መረጃ እናያለን፡፡
የስኳር ህመም አንድ ሰው አለው ስንል በደሙ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን መሆን ከሚገባው በላይ ከፍ ብሏል ማለት ነው።
ይህ ህመም አብዛኛውን ጊዜ በሂደት እና ከብዙ አመታት በኋላ የሚከሰት ነው፤ በመሆኑም ዕድሜያቸው ከ40 በላይ የሆኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ሲጠቁ ይታያል።
ህመሙ ህጻናትና ወጣቶችም ላይም ሊከሰት ይችላል፤ በሽታው በተለይም ክብደታቸው ከፍ ያለ እና አዘውትረው የአካል እንቅስቃሴ የማያደርጉ ሰዎችን የሚያጠቃ ነው፡፡
በተሻለ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ግለሰቦች በስኳር በሽታ የመጠቃት ዕድላቸው ከፍ ያለ ነው።
ሌላኛው ደግሞ ሰውነታችን የተመረተውን ኢንሱሊን በአግባቡ መቀበል ሳይችል ሲቀር ወይም ሁለቱም ባንድ ላይ ሲከሰት የስኳር በሽታ ይፈጠራል።
የሚፈጠረው ኢንሱሊን ምንድንነው ?
ምግብ ስንበላ ሰውነታችን ምግቡን ወደ ስኳር የሰውነታችን ጣፊያ ኢንሱሊን የሚባለውን ነገር ያመነጫል፤ ይህ ኢንሱሊን የሰውነታችን ህዋሶችእንዲከፈቱ በመርዳት የተመረተው ግሉኮስ (ስኳር) ወደ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ለሀይል ምንጭ እንድንጠቀምበት ይረዳል።
በዓለምአቀፍ ደረጃ በአሁኑ ሰዓት 380 ሚሊዮን ህዝቦች በስኳር በሽታ ተይዘው ይገኛሉ።
የዓለም ጤና ድርጅት እንደገመተው ከሆነ በ2030 ይህ ቁጥር በእጥፍይጨምራል።
ከጤና መረጃ ድረገጾች እንዳገኘነው መረጃ ከሌሎች በሽታዎች በበለጠ የስኳር በሽታ ለአይነ ስውርነት፣ ለኩላሊትሥራ ማቆም እና ለልብ በሽታ ዋና መንስኤ ሆኖ ይገኛል።
ሁለት የስኮር ህመም አይነቶች አሉ እነሱን ስንመለከት፦
አይነት አንድ (Type 1) የስኳር በሽታ በጣም ከባዱ የስኮር በሽታ አይነት ሲሆን ከኢንሱሊን አመራረት ጋር የተያያዘ ነው። አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው በሕጻንነትና በጉርምስና ጊዜ ነው፤ ሆኖም ግን በሌላ የእድሜ ክልል ውስጥ አይከሰትም ማለት አይደለም።
አይነት ሁለት (Type 2) የስኮር በሽታ ሁለተኛው አይነት የስኳር በሽታ ደግሞ ከኢንሱሊን ጋር ብዙም ያልተያያዘ ሲሆን ብዙውን ጊዜ የሚያጠቃው ከ35 ዓመት በላይ ያሉ ጎልማሶችን ነው። በዚህ በሽታ የተጠቁ ህመምተኞች ከፊሉን ለሰውነታቸውን የሚያስፈልገውን ኢንሱሊን ማምረት የሚችሉ ሲሆን ችግሩ ብዙውን ጊዜ የኢንሱሊኑ መጠን በቂ ሆኖ አለመገኘቱ ነው።
የስኳር ህመም ምልክቶች
ቶሎ ቶሎ ሽንት መምጣት፣ ከባድ የሆነ ጥማት፣ ከባድ የሆነ ራሃብ ፣ ድንገተኛ የክብደት መጨመርና የክብደት መቀነስ፣ የተቆረጠ ወይም የተቀደደ የሰውነት ክፍል ቶሎ አለመዳን፣ስሜት አልባ መሆን፣የዕይታ መጠን መቀነስ (ብዥ ማለት)፣ የመሳሰሉት ናቸዉ፡፡
የስኳር ህመም መከላከያ መንገዶች
የተስተካከለ የአመጋገብ ስርዓት መኖር፣ ክብደታችንን መከታተል፣ እንቅስቃሴ (ስፖርት) መስራት፣ ከካፌ ወይም ሬስቶራንቶች የሚወጡ ‘ቴክ አዌይ’ አለማብዛት (ቤት ውስጥ አዲስ ነገሮችን መስራትና መጠቀም)
መጠጥ እና ሲጋራ ማቆም፣ የደም ግፊትን መከታተል፣ በየጊዜው በዶክተር መታየት ይጠቀሳሉ፡፡
በሜሮን ንብረት