ከአሜሪካ ጀርባ ከግብጽ ጋር ያሴሩት ሴናተር ክስ ተመሰረተባቸው

1 Yr Ago 600
ከአሜሪካ ጀርባ ከግብጽ ጋር ያሴሩት ሴናተር ክስ ተመሰረተባቸው

በአሜሪካ ኒው ጀርሲ ሴናተር የሆኑት ሮበርት ሜኔንዴዝ በሴናተርነት ስራቸው ለሁለተኛ ጊዜ በፌዴራል ፍ/ቤት የሙስና ክስ እንደቀረበባቸው በትናንትናው ዕለት በርካታ መገናኛ ብዙሀን በፊት ገጻቸው ይዘውት ወጥተዋል። 

 ሜኔንዴዝ፣ ባለቤቱ እና ሌሎች ሶስት ሰዎች በጉቦ የተከሰሱ ሲሆን ሜኔንዴዝ የተለያዩ አካላት ጉዳያቸው ተደማጭነት እንዲያገኝ የሚሰጧቸውን ጉቦ ሲቀበሉ ነበር ተብሏል።

 ሮበርት ሜኔንዴዝ  ከቀረቡባቸው ውንጀላዎች መካከል “የግብፅን መንግስት በሚስጥር ሲደግፉ እና ለግብፅ ባለስልጣናት ሚስጥራዊ መረጃዎችን ሳይቀር በማቀበል በአሜሪካ ሴኔት ያላቸውን የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ሃላፊነት አላግባብ መጠቀማቸው ተገልጿል።

 ለአብነትም ሴናተሩ ከሴራ አጋሮቹ አንዱ ከሆነው ግብፃዊው ነጋዴ ዋኤል ሃና ጋር በግል ጥቅማ ጥቅሞች በመስማማት በምትኩ ለግብፅ ከፍተኛ መጠን ያለው ወታደራዊ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደርግ አድርገዋል።

 ግብፃዊው ነጋዴ ዋኤል ሃና በ2018 ከሴናተሩ ጋር እራት ከተመገቡ በኋላ ለአንድ ግብጻዊ ባለስልጣን በግብጽ ላይ የተጣሉ አነስተኛ የጦር መሳሪያዎች እና ተተኳሾች ድጋፍ እገዳ ተነስቷል ሲሉ መልዕክት መላክቸው መረጋገጡን መርማሪዎች ገልጸዋል።

 በዚያው ወር መገባደጃ ላይ፣ የሜኔንዴዝ ሚስት ለግብፅ የሚደረገውን እርዳታ ለመጠየቅ ለሴናተሮች የተላከውን ደብዳቤ በድጋሚ እንዲያስተካክሉ ለአንድ የግብፅ ባለስልጣን መልዕክት እንደላኩ ምርመራው አጋልጧል።

 ሜኔንዴዝ የግብፅ መንግስት የጻፈው አስመስሎ ግብጽ ታግዶባት የነበረው የ300 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እንዲደረግላት የሚጠይቅ ደብዳቤ ከፃፈ በኋላ ከግል ኢሜይል አካውንቱ ወደ ባለቤቱ አካውንት ልኳል። ባለቤቱም ይህን የኢሜይል መልዕክት ለግብጻዊው ነጋዴ ሃና አስተላልፋለች። ከዚያም ሜኔንዴዝ እና ሚስቱ ኢሜይሎችን በመሰረዝ ጉዳዩን ለመደበቅ ሞክረዋል ይላል ዋሽንግተን ፖስት በዘገባው ይዞት የወጣው የመርማሪዎች ሪፖርት።

 ሜኔንዴዝ ከዋኤል ሃና ጋር በመመሳጠር ጭምር  ነጋዴው ከግብፅ ወደ አሜሪካ ብቸኛው ስጋ አስመጪ እንዲሆን ስልጣኑን ተጠቅሞ ረድቶታል።

 እ.ኤ.አ. በ 2019 የአሜሪካ ግብርና ዲፓርትመንት ለዋኤል ሃና የተሰጠውን በብቸኝነት ስጋ ከግብጽ የማስመጣት መብት አገደ። ታድያ ይህ ውሳኔ መተላለፉን ተከትሎ ሜኔንዴዝ ከዋኤል ሃና እና ከግብፃዊ የስለላ ሰራተኛ ጋር በዋሽንግተን ዲሲ ተገኛኝተው መከሩ። ከዛም ከሁለት ቀናት በኋላ ሜኔንዴዝ የግብጻዊው ነጋዴ ዋኤል ሃና ንግድ ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ከግብርና ዲፓርትመንት ባለስልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ የዋኤል ሃና ከግብጽ ብቸኛ ስጋ አስመጭነት መቀጠሉን ይኸው የመርማሪዎች ሪፖርት ያሳያል።

 በዚያው ሰሞን ዋኤል ሃና ለሜኔንዴዝ ባለቤት 23ሺህ ዶላር የሞርጌጅ ክፍያ መክፈሉን የሚያሳይ መረጃም ወጥቷል።ሜኔንዴዝ ዋኤል ሃናን “ከግብፅ ፕሬዚዳንት የበለጠ ኃያል ትሆናለህ” ይሉት እንደነበርም ነው መረጃዎቹ የሚያሳዩት።

 በክሱ መሰረት በ2022 ኤፍቢአይ የሜንዴዝ ቤት ላይ ፍተሻ ባደረገበት ጊዜ ከ480ሺህ ዶላር በላይ ጥሬ ገንዘብ በልብስ፣ ቁም ሳጥን፣ ካዝናዎች ውስጥ ተደብቀው አግኝቷል። ከዚህ ባለፈም ከ100ሺህ ዶላር በላይ የሚያወጡ የወርቅ ጥፍጥፎች በሴናተሩ ቤት ውስጥ መገኘታቸው ተገልጿል።

 ከዚህ ባለፈም ሴናተሩ በባለቤታቸው በኩል ገንዘብን ሲያሸሹ እና እንደ ሜርሴዲስ ቤንዝ ያሉ ቅንጡ መኪኖችን ሲገዙ መሰንበታቸውንም ይህ ምርመራ አጋልጧል።

 ሜኔንዴዝ እ.አ.አ. በ2024 በድጋሚ ለመመረጥ በእንቅስቃሴ ላይ ሲሆኑ የቀረበባቸውን ክስ ተከትሎ ከውድድሩ አስቀድሞ መቀመጫውን እንዲለቅ ከፍተኛ ጫና ገጥሟቸዋል።

በሰለሞን ከበደ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top