የደቡብ አሜሪካ ሀገራት በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ላይ ለምን ገለልተኛ አቋም ያዙ?

1 Yr Ago 175
የደቡብ አሜሪካ ሀገራት በሩሲያ እና በዩክሬን ጦርነት ላይ ለምን ገለልተኛ አቋም ያዙ?

ብዙ የምዕራባውያን ሀገራት ሩሲያ ላይ ማዕቀብ በመጣል እና የጦር መሳሪያዎችን ደግሞ ለዩክሬን በማቅረብ ጦርነቱ ላይ ተሳትፎ እያደረጉ ቢሆንም፣ አብዛኛው የደቡብ አሜሪካ ሀገራት ግን በጦርነቱ ላይ የተለየ አካሄድ መከተላቸው ይገለፃል።

እንደ ኩባ እና ሜክሲኮ ያሉ አገሮች ቀደም ሲል የአሜሪካ እና የምእራባውያን ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጣልቃገብነት በሀገሮቻቸው ላይ ባስከተለው ጥቁር ጠባሳ ምክንያት ገለልተኛ አቋም መያዛቸው ይጠቀሳል።

በአንፃሩ ሌሎች የቀጠናው ሀገራት ከዚህ ቀደም ተከስተው በነበሩ ወረራዎች እና ጦርነቶች ምክንያት የደረሰባቸው ኢኮኖሚያዊ ጫና ከግምት ውስጥ በማስገባት ከምዕራባውኑ የተለየ መንገድ መምረጣቸው ይነገራል፡፡

በኒው ላይን ኢንስቲትዩት ከፍተኛ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ዩጂን ቻውሶስኪ እንደሚሉት ደቡብ አሜሪካ በአብዛኛው የሚወክለው "አለምአቀፍ የደቡብ አቋም" መሆኑን ገልፀው፤ ይህ ቀጠና ደግሞ የዩክሬን ጦርነትን በተመለከተ በግልፅ የምዕራባውያንም ሆነ የሩሲያ ደጋፊ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

አብዛኞቹ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት የዩክሬን ጦርነት ወደ አዲስ የቀዝቃዛ ጦርነት ሊገባ እንደሚችል ስጋት ኣላቸው የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ፤ የምዕራቡን ዓለም የቅኝ ግዛት አስከፊ ታሪክ ለተመለከቱት እና አሁንም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ለሚገኙት የደቡብ አሜሪካ አገሮች ሁኔታው ከባድ መሆኑን ያነሳሉ።

ለአስርት አመታት በዘለቀው የቀዝቃዛ ጦርነት ወቅት፣ የደቡብ አሜሪካ ሀገራት በአሜሪካ የሚደገፉ በርካታ መፈንቅለ መንግስቶች እንዳጋጠሟቸው የሚጠቀሱት ቻውሶስኪ፤ በዚህም  ሀገራቱ አስከፊ ዋጋ መክፈላቸውን ይገለጻሉ፡፡

አሁን ላይ እንደ ብሪክስ ያሉ ቡድኖች ለደቡብ አሜሪካ አገሮች የበለጠ ጥቅም አላቸው የሚሉት የፖለቲካ ተንታኙ፤ አርጀንቲና በቅርቡ ከሳውዲ አረቢያ እና ከተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ጋር በመሆን ብሪክስን መቀላቀሏ ለዚህ እንደ አብነት የሚጠቀስ መሆኑን ያነሳሉ።

የፖለቲካ ተንታኙ ዩጂን ቻውሶስኪ ለቲአርቲ ዎርልድ አንደለገፁት ብራዚል በብሪክስ በኩል የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት እንዲቆም እራሷን እንደ ገለልተኛ አስታራቂ አድርጋ ማቅረቧም የደቡብ አሜሪካ ሀገራት በጦርነቱ ላይ ያላቸውን አቋም በግልፅ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top