የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳትፎ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተደማጭነት ለማሳደግ ያስቻለ ነው፡- አምባሳደር መለስ ዓለም

10 Mons Ago
የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳትፎ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ያላትን ተደማጭነት ለማሳደግ ያስቻለ ነው፡- አምባሳደር መለስ ዓለም

በኒው ዮርክ እየተካሄደ ባለው 78ተኛው የተባበሩት መንግስት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሻለ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር መቻሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ገለጹ።

ጉባኤው "ሰላም፣ብልፅግና፣ለውጥና ዘላቂነት" በሚል መሪ ሀሳብ በመከናወን ላይ ይገኛል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከጉባኤው ጎን ለጎን 30 ከሚሆኑ የአገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የተመድ የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን አምባሳደር መለስ ዓለም ገልጸዋል።

በውይይቶቹ አገራት፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አጋር አካላት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በጎ ግንዛቤ እንደያዙና የልማት አጋርነትና ትብብር ጎልቶ መታየቱን አመልክተዋል።

ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያን ለመደገፍ ያሳዩት ፍላጎት አበረታች እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ጉባኤው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ያላትን ተደማጭነት ከማሳደግ አኳያ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል ነው ያሉት አምባሳደር መለስ።

ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ ከራሷ ባለፈ ለአፍሪካና ሌሎች አዳጊ አገራት ድምጽ መሆን መቻሏን ተናግረዋል።

በጀርመን መራሔ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ በተጠራው መደበኛ ያልሆነ ስብሰባም ኢትዮጵያ አፍሪካ በተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ማግኘት አለባት የሚለውን የአህጉሩን የጋራ አቋም ማንጸባረቋን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ በጠቅላላ ጉባኤው ያከናወነችው የሁለትዮሽና የባለ ብዙ ወገን ዲፕሎማሲ ስራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት እቅድ እንዲሁም ወዳጆችን የማብዛትና አጋሮች የማበራከት ስራ አካል መሆኑን ነው አምባሳደሩ ያብራሩት።

በአጠቃላይ በጉባኤው ላይ የኢትዮጵያን እውነታና አቋም ከማስረዳት አኳያ እንዲሁም የሁለትዮሽ፣ ቀጣናዊና የባለ ብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ስራዎች ስኬታማ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ነገ የኢትዮጵያንና የመንግስታቸውን አቋም የሚገልጽ ንግግር ለጠቅላላ ጉባኤው ያደርጋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top