የ2030ውን ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ሴቶችን በሁሉም የኅብረተሰብ ሕይወት ውስጥ ተሳታፊ ማድረግ የግድ አስፈላጊ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት "ለሴቶች የፋይናንስ ተሳትፎን ማመቻቸት፦ ግንዛቤ እና ትምህርት ከኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በቀረበው መርሐ-ግብር ላይ ነው።
አቶ ደመቀ በዚሁ በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ በተዘጋጀው እና የተመድ አባል ሀገራት እንዲሁም የተመድ ድርጅቶች ተወካዮች በተገኙበት በቀረበው ዝግጅት ባደረጉት ንግግር “ኢትዮጵያ የተከተለችው ሴቶችን በአግባቡ የማሳተፍ ፖሊሲ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ አቅም ለመጠቀም ወሳኝ ሚና ተጫውቷል” ብለዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የፋይናንስ አካታችነትን ተግባራዊ በማድረግ ቀጣይነት ያለው ዕድገትን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኑንም ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።
የተመድ ሴቶች ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሞኤዝ ዶራይድ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ይህንን ተነሣሽነት በመውሰዷ አመስግነው፣ የዲጂታል ግንኙነትን ማረጋገጥም አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።