በ2011 ዓ.ም በነቀምቴ ከተማ ይፋ የተደረገው “የነቀምቴ አዋጅ” በቡና ምርት እና ጥራት ረገድ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል፦ አቶ ሽመልስ አብዲሳ

10 Mons Ago
በ2011 ዓ.ም በነቀምቴ ከተማ ይፋ የተደረገው “የነቀምቴ አዋጅ” በቡና ምርት እና ጥራት ረገድ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል፦ አቶ ሽመልስ አብዲሳ

በ2011 ዓ.ም በነቀምቴ ከተማ ይፋ የተደረገው “የነቀምቴ አዋጅ” በቡና ምርት እና ጥራት ላይ ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ።

የኢኮኖሚ ንቅናቄን እንዲያነቃቁ ከተቀረጹ አዳዲስ እርምጃዎች መካከል አንዱ የቡና ልማት መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በ“የነቀምቴ አዋጅ” የተቀሰቀሰው መነቃቃት የቡና ምርት በመጨመርም ሆነ የምርት ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ተጨባጭ ውጤት አስገኝቷል ብለዋል።

በ2011 ዓ.ም 997 ሚሊዮን የቡና ችግኝ በመትከል ንቅናቄው መጀመሩን እና በ2015 ዓ.ም ደግሞ 1.33 ቢሊዮን የቡና ችግኝ ለመትከል መቻሉን ገልጸዋል።

ይህም በአምስቱ ዓመታት ውስጥ የተተከለውን የቡና ችግኝ 5.4 ቢሊዮን ያደርሳል ብለዋል።

በዚህ አፈጻጸም ሁለት ሚሊየን ሔክታር የነበረው የቡና ተክል ሽፋን ከ2.9 ሚሊዮን ሔክታር በላይ ማድረስ መቻሉን ነው የገለጹት።

በዚህ ጊዜ ከነበረው የቡና ልማት ሽፋን፣ ምርት ይሰጥ የነበረው 966 ሺህ ሔክታሩ ብቻ ሲሆን በተደረገ ርብርብ በ2015 ዓ.ም ወደ 1.31 ሚሊዮን ሔክታር ማድረስ መቻሉን የገለጹት አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ በ2016 ዓ.ም ደግሞ 1.45 ሚሊዮን ሔክታር ለማድረስ እየሠራን እንገኛለን ብለዋል።

የምርት ጭማሪ በሚመለከት፣ 2011 ዓ.ም 6.5 ሚሊዮን ኩንታል የነበረውን ዓመታዊ ምርት በ2015 ዓ.ም ወደ 10.4 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ መቻሉን እና በ2016 ዓ.ም ደግሞ ወደ 11.4 ሚሊዮን ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ እየተተገበረ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በዚህ ረገድ ያደረገው የተቀናጀ ንቅናቄ ውጤት አልባ አልነበረም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በ2015 ዓ.ም ለውጭ ገበያ ከቀረበ የቡና ምርት ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ቢሊዮን ዶላር የተሻገረ (1.3 ቢሊዮን) ገቢ መገኘቱን እና ከዚህ አቅርቦት ውስጥ የክልሉ ድርሻ ወደ 70% የተጠጋ እንደነበር በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል። 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top