ኢትዮጵያ በ78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ እያከናወነች ነው፦ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ

2 Mons Ago
ኢትዮጵያ በ78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ እያከናወነች ነው፦ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ

ኢትዮጵያ በአሜሪካ ኒው ዮርክ እየተካሄደ ባለው 78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ሥራ እየሠራች መሆኑን በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ገለጹ።

78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ "ሰላም፣ ብልጽግና፣ ለውጥ አና ዘላቂነት" በሚል መሪ ሐሳብ በመከናወን ላይ ይገኛል።

በተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ ኢትዮጵያ በጉባዔው ያላትን ተሳትፎ አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም ኢትዮጵያ ከዋናው ጉባዔው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ውይይት ማድረግ መቻሏን ጠቁመዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተለያዩ ሀገራት ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር መምከራቸውን ጠቁመዋል።

ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና አጋር አካላት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ፣ በቀጣናዊ እና በባለብዙ ወገን የትብብር ጉዳዮች ውይይት ማድረጋቸውንም ነው ያስረዱት።

በዚህም ሀገራቱ ኢትዮጵያ የጀመረችው የለውጥ ጉዞ እና የሰላም ሂደት በትክክለኛ አቅጣጫ እየሄደ መሆኑን የጋራ መግባባት ተፈጥሮበታል ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራት እና ተቋማት በተዘጋጁ የጎንዮሽ የውይይት መድረኮች ተሳትፎ በማድረግ ያላትን አቋም ማስረዳቷንም ገልጸዋል።

በዚህም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ እና አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት ድምጿን ማሰማቷን ተናግረዋል።

በተለይም በጠቅላላ ጉባዔው ኢትዮጵያ ያላትን እውነታ በሚገባ ማስረዳት እና አቋሟንም በትክክል ማንፀባረቅ መቻሉን አመልክተዋል።

ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና የተለያዩ ኩባንያዎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የተደረጉ ውይይቶች ፍሬያማ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዓለም አቀፍ ተቋማት የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ እና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን ለማፍሰስ ያሳዩት ፍላጎት ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በሀገር አቀፍ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ያላትን ምልከታ እና አቋም የምታንፀባርቅበት የፖሊሲ ንግግር በጠቅላላ ጉባዔው ላይ እንደምታደርግ መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአሜሪካ ኒው ዮርክ እየተካሄደ ያለው 78ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ እስከ መስከረም 15 ቀን 2016 ዓ.ም የሚቆይ ይሆናል። 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top