ከስድስት አስርተ ዓመታት በላይ በማዕቀብ ስር በቆየችው ኩባ የተካሄደው የቡድን 77 ጉባኤ ለሀገሪቷ ምን ፋይዳ ይኖረው ይሆን?

1 Yr Ago 136
ከስድስት አስርተ ዓመታት በላይ በማዕቀብ ስር በቆየችው ኩባ የተካሄደው የቡድን 77 ጉባኤ ለሀገሪቷ ምን ፋይዳ ይኖረው ይሆን?

ቡድን 77 በተባበሩት መንግስታት የንግድ እና ልማት ኮንፈረንስ (UNCTAD) በ1964 የተመሰረተ የታዳጊ ሀገራት ጥምረት ነው። ቡድኑ በ77 አባል ሀገራት የጀመረ ሲሆን አሁን ላይ 134 የሚሆኑ የአፍሪካ፣ የእሲያ፣ የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ሀገራትን ያጠቃልላል። ቡድኑ የፖለቲካ ነፃነት እንዲኖር በማድረግ እና በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላቸውን ሚና እና ተፅዕኖ ለማሳደግ የሚያስችል ዓላማን ሰንቆ የተፈጠረ ጥምረት ነው።

የቡድኑ አባል ያልሆነችው ቻይና “ቡድን 77 እና ቻይና” በሚል ጥምረት ስር ለቡድኑ ድጋፍ እና ትብብር ስትሰጥ ቆይታለች። በቡድን 77 እና ቻይና ጥምረት ውስጥ ከሚገኙ 134 ከሚሆኑት ሀገራት ውስጥ አንዷ የሆነችው ኩባ ከ60 ዓመታት በፊት በአሜሪካ የተጣለባትን ማዕቀብ ተቋቁማ ቆይታለች።

በስፔን ቅኝ ግዛት ስር የነበረችዋ ኩባ ስፔን ከአሜሪካ ጋር ባደረገችው ጦርነት በአሜሪካ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ስፔን ተሸንፋ ስትወጣ እ.አ.አ ከ1898 ዓ.ም ጀምሮ ኩባ በአሜሪካ በይዞታነት ቆይታለች። ኩባ እ.አ.አ በ1902 ከአሜሪካ አስተዳደር ተገንጥላ ነፃ ከሆነች በኋላም አሜሪካ በኩባ ላይ የነበራት የበላይነት የቀጠለ ሲሆን፣ አሜሪካም በኩባ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ መግባቷም አላቋረጠችም ነበር።

እ.አ.አ በ1956 እስከ በ1959 በተደረገው ጦርነት የአብዮቱ መሪ ፊደል ካስትሮ ተሳክቶላቸው በአሜሪካ የሚደገፈውን በፉልጌንሲዮ ባቲስታ የሚመራውን የኩባ አገዛዝ አስወግደው ከሶቪየት ኅብረት ጋር በወዳጅነት የተሳሰረ የሶሻሊስት መንግሥት አቋቋሙ። ኩባ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአሜሪካ ጥርስ ስር የገባች ሲሆን ከዚህም ጋር በተያያዘ አሜሪካ በኩባ ሪፐብሊክ ላይ ተደጋጋሚ የኢኮኖሚ ማዕቀቦችን ጥላለች።
እ.ኤ.አ. በየካቲት 1962 ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ የኩባ መንግሥት ለወሰዳቸው እርምጃዎች ምላሽ ለመስጠት በአሜሪካ እና በኩባ መካከል ባለው የንግድ ልውውጥ ላይ ማዕቀብ ከጣለች ጊዜ አንስቶ በሁለቱ ሀገራት ያለው ግንኙነት እስካሁን ድረስም እየታመሰ ይገኛል።

እ.ኤ.አ. በ1982 የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ሮናልድ ሬጋን ኩባን የማዕከላዊ አሜሪካ እና የአፍሪካ ሽብርተኞችን ትደግፋለች በማለት የሽብርተኝነት ደጋፊ በማለትም ሰይመዋታል። ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ እና ቢል ክሊንተን እ.አ.አ በ1992 የኩባ ዲሞክራሲ ህግ እና የ1996 የኩባ ነፃነት እና ዲሞክራሲያዊ አንድነት ህግ፣ የሄልምስ-በርተን ህግ በመባል የሚታወቁትን ህጎች የተፈራረሙ ሲሆን ይህም የአሜሪካን ማዕቀብ ያጠናከረ እና ኩባ የህዝቧን ነፃነት ወደ የሚያስከብር ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እስክትሸጋገር ድረስ እገዳው እንደሚቆይ አሜሪካ ገልፃለች።

ኩባ ከማንኛውም ሀገር በላይ ማዕቀብ የተጣለባት ሀገር ስትሆን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ፣ በወንድማቸው ፊደል ካስትሮ ወንበር ከተተኩት የኩባው መሪ ራውል ካስትሮ ጋር በመገናኘት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ አንዳንድ እርምጃዎችን ቢወስዱም ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኩባ ላይ አዲስ ማዕቀብ በመጣል በሀገራቱ መሀል የተጀመረውን መሻሻል ወደ ነበረበት መልሰዋል። በአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ደግሞ አንዳንድ ማዕቀቦችን በጥቂቱም ቢሆን ለማቅለል ተችሏል።

ለዓመታት በካስትሮ ቤተሰብ ስትመራ የነበረችዋ ኩባ እ.ኤ.አ በ2018 የኮሚኒስት አባል የሆነው ሚጌል ዲያዝ የኩባ ፕሬዝዳንት የነበሩትን የፊደል ካስትሮ ወንድም ራውል ካስትሮን በመተካት የሀገሪቷ ፕሬዚዳንት ለመሆን በቅተዋል።

ኩባ የመንግሥት ለውጥ ብታደርግም ኢኮኖሚዋ ግን ምንም መሻሻል እንዳልታየበት የተለያዩ ምንጮች ያሳያሉ። ለውጥ እንዳታሳይም ካደረጉት ነገሮች አንዱ ለዘመናት የቆየው እና በየጊዜው እየከረረ እና እየታደሰ የመጣው የአሜሪካ ማዕቀብ ሲሆን፣ በዚህ ሁኔታ የሀገሪቷን እድገት አቀንጭረው የሚያስቀሩ ማዕቀቦች ተጥለውባትም ከ60 ዓመት በላይ ኖራለች።

በአሜሪካ የንግድ ድርጅቶች እና በአሜሪካ ህግ የተደራጁ ወይም በአሜሪካ ዜጎች ባለቤትነት የተያዙ የንግዶች ተቋማት ከኩባ ጋር የሚያደርጉትን የንግድ ልውውጥ የሚከለክል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የንግድ እገዳ ተጥሎባት ቆይታለች። ይህም የሀገሪቷን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቶታል። 70 በመቶ የሚሆነውን ምግቧን ከውጪ የምታስገባዋ ኩባ የሀገሪቷ የዋጋ ግሽበት በላቲን አሜሪካ እና በካሪቢያን አካባቢ ካለው ከፍተኛው እንደሆነ እና በየጊዜውም እየጨመረ መምጣቱ ህዝቡን ለአመፅ እና ለስደት ሲዳርገው ቆይቷል።

ኩባውያን በሀገሪቷ ውስጥ ካለው የኢኮኖሚ ትርምስ ለማምለጥ ስደትን የመረጡ ሲሆን እ.አ.አ ከ2021 የበጀት ዓመት ጀምሮ 374 ሺህ ኩባውያን ወይም 3 በመቶ የሚሆነው የደሴቱ ህዝብ ወደ አሜሪካ ሊገቡ ሲሉ በደቡባዊ አሜሪካ ድንበር ላይ እንደተያዙ የውጭ ጉዳይ ምክር ቤት ያመላክታል፤ ይህ ፍልሰትም በኩባ ታሪክ በአስርተ ዓመታት ውስጥ ያልታየ ትልቁ ፍልሰት መሆኑ ተገልጿል።

ቡድን 77 ባደጉ ሀገራት በማደግ ላይ ባሉት ላይ የሚደረገውን ጫና ለመቀነስ ብሎም ለማስቆም የሚያስችሉ ሀሳቦችን ዓላማው አድርጎ ሲነሳ፣ የአባላቱን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስተዋወቅ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ እንደ አንድ ቡድን የመከራከር አቅማቸውን በማጠናከር ጥቅማቸውን ለማስከበር ለማስቻል ያለመ ነው።

ቡድኑ ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ በተለያዩ ጊዜያት ኩባን የተመለከቱ አጀንዳዎች ተነስተዋል፤ ለአብነትም እ.ኤ.አ በ2005 በተካሄደው የቡድን 77 ጉባኤ ላይ የቡድኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አሜሪካ በሶሪያ እና በኩባ ላይ የጣለችው ማዕቀብ አውግዘው ነበር።

እ.ኤ.አ በ2022 በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በኢኮኖሚ ቀውስ ላይ የምትገኘዋ ኩባ አሜሪካ የጣለችባትን ማዕቀብ እንድታነሳላት የጠየቀችውን ጥያቄ በመደገፍ በእገዳው ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞ ሲያሰሙ፣ በጉባኤው ላይ ከነበሩ ሀገራት 185 የሚሆኑት እገዳውን ሲያወግዙ አሜሪካ እና እስራኤል እገዳውን በመደገፍ ሲቃወሙ፣ ብራዚል እና ዩክሬን ድምፀ ታቅቦ አድርገዋል።

በዚህ በያዝነውም ዓመት በኩባ ሃቫና በተካሄደውም 18ኛው የቡድን 77 ጉባኤ ላይ የኩባው ፕሬዝዳንት ሚጌል ዲያዝ ካኔል በስብሰባው መክፈቻ ላይ፣ "ሰሜናዊው ዓለም የተቀረውን ዓለም እንደ ፍላጎቱ እና እንደሚመቸው አደራጅቷል፤ ከዚህ በኋላ የደቡቡ ዓለም የጨዋታውን ህግ መቀየር ይኖርበታል" ሲሉ ተሰምተዋል። አክለውም፣ በዓለም ላይ እየታየ ላለው ቀውስ እና የዓለም ሙቀት መጨመር ዋና ተጠቂዎች ታዳጊ ሀገራት ናቸውም ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ዲያዝ ካኔል በኒውዮርክ በተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ቡድን 77 ለዘመናት የዘለቀ ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን እና ችግሮችን ለመጠገን ያለመ እንደሆነ ገልፀው፣ ግቦቹን እውን ለማድረግ የታዳጊ ሀገራት ጥረቶች በቂ ባለመሆኑ ለገበያ ተደራሽነት፣ ፍትሃዊ የፋይናንስ ሁኔታ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የሰሜን - ደቡብ ትብብር በተጨባጭ ተግባራት መደገፍ እንዳለበት አሳስበዋል።

እንደ ብሪክስ እና ቡድን 77 ያሉ ከጊዜ ወዲህ እየተስፋፉ ያሉ ቡድኖች በኃያላን ሀገራ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ብሎም የአባል ሀገራቱን እድገት ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍትሀዊና ለሁሉም የሚጠቅም እድገትን ለማስፈን፣ እንዲሁም በአባል ሀገራቱ መካከል ያለውን ትብብር ማሳደግ ፣ማስፋፋት እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተፅዕኗቸውን መጨመር ዋና ዓላማቸው አድርገው እየተጓዙ ነው፡፡

80 በመቶ የሚሆነውን የዓለም ህዝብ የሚወክል፣ በማደግ ላይ ያሉ እና ታዳጊ ሀገራት ስብስብ የሆነው የቡድን 77 እና ቻይና ጥምረት አባል የሆነችው ኩባም ቡድኑ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት በኢኮኖሚ እና በተለያዩ ዘርፎች በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተፅኖውን ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረት ተጠቃሚነቷ እስከዚህም የሚባል ሲሆን፣ ሀገሪቷ ከገባችበት ማጥ ውስጥ እንድትወጣ በቡድኑ የሚደረገው ጥረት ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል። በአንድ ፓርቲ ኮሚኒስት መንግስት የምትመራው ኩባ ደሴት አሁንም ከ1962 ጀምሮ በተጣለባት የአሜሪካ ማዕቀብ ቀንበር ስር ትገኛለች።

በሶስና ምንዳ

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top