በ1868 በአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ከመቅደላ ተዘርፈው የተወሰዱ የተለያዩ ቅርሶች በለንደን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ተመልሰዋል።
ከተመለሱት ቅርሶች መካከል የመድሃኒዓለም ታቦት፣ የልዑል ዓለማየሁ የጸጉር ዘለላ፣ ከብር የተሰሩ እና በነሃስ የተለበጡ ሶስት ዋንጫዎች እንዲሁም በዘመኑ ጦርነት ላይ የዋለ የጦር ጋሻ ይገኙበታል።
በርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ በብሪታኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈሪ መለሰ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑካን ቡድን፣ የብሄራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ ተወካይ፣ የብሪታኒያ ፓርላማ አባላት፣ ቅርሶቹን ለማስመለስ የተባበሩና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
አምባሳደር ተፈሪ መለሰ፣ የተመለሱት ቅርሶች ለኢትዮጵያ ህዝብ ሃይማኖት፣ ታሪክ እና ባህላዊ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው ብለዋል።
አሳዛኝ በሆነው የመቅደላ ጦርነት ምክንያት የተዘረፉ የኢትዮጵያ ቅርሶች እስካሁን አለመመለሳቸው በመላው ኢትዮጵያዊ ልብና አዕምሮ ውስጥ ጥያቄ ፈጥሮ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
እነዚህ ቅርሶች የአንድ ጥንታዊት ሀገር የታሪክ፣ የባህልና የማንነት መገለጫዎች ናቸው ብለዋል።
የተመለሱት ቅርሶች በተገቢው ቦታቸው እንዲቀመጡ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚላኩም አረጋግጠዋል።
የብሄራዊ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል አሉላ ፓንክረስት (ፕ/ር) በበኩላቸው፣ ቅርሶች የሚመለሱበት ሁኔታ ይበልጥ መጠናከር እንዳለበት ተናግረዋል።
የብሪታኒያ ፓርላማ አባል ሎርድ ፖል ቦቲንግ፣ ጥንታዊ እና ታሪካዊ የሆነቸው ኢትዮጵያ የማንነቷ መገለጫ የሆኑ ቅርሶቿ እንዲመለሱ ጥረት ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል።
በዛሬው ዕለት የተደረገው ርክክብ ተገቢ ተግባር መሆኑን ጠቁመው፣ በቀጣይ የብሪታኒያ ሙዚዬሞች ከኢትዮጵያ የተዘረፉ ቅርሶችን ባለቤቱ ለሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲመልሱ ጥሪ ማቅረባቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልዑክን የመሩት መጋቢ ሀዲስ ቀሲስ አባተ ጎበና እንደተናገሩት፣ በ1868 ከመቅደላ የተዘረፈው የመድሃኒያለም ታቦት እንዲመለስ መደረጉ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላቅ ያለ ሃይማኖታዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸው ፣ ታቦቱ በተገቢው የሃይማኖት ስርዓት ተይዞ ወደ ሀገሩ በቅርቡ እንደሚገባ ገልጸዋል።