6 ፖርቹጋላዊያን ወጣቶች 32 የአውሮፓ ሀገራትን ፍርድ ቤት ከሰሱ

10 Mons Ago
6 ፖርቹጋላዊያን ወጣቶች 32 የአውሮፓ ሀገራትን ፍርድ ቤት ከሰሱ
6 ፖርቹጋላዊያን ወጣቶች የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር ሀላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም በሚል 32 የአውሮፓ ሀገራትን ፍርድ ቤት ከሰዋል፡፡
 
ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ለታዳጊዎች እና ወጣቶች ቀጣይ ህልውና ተገቢውን ትኩረት አልሰጡም በሚል ከተከሰሱት ሀገራት መካከል ዩናይትድ ኪንግደም፣ ሩሲያ፣ ተርኪዬ፣ ኖርዌይ እና ሲውዘርላንድ ይገኙበታል፡፡
 
ክሱ የቀረበው ለአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ሲሆን ይሄን ያህል ቁጥር ያላቸው የአንድ አህጉር አባል ሀገራት በአንድ መዝገብ ሲከሰሱ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑንም አል ጃዚራ ዘግቧል፡፡
 
መጻኢ ህልውናችንን አደጋ ላይ ጥለዋል በሚል ሀገራቱን ከከሰሱት ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነችው ክላውዲያ ዱዋርቴ፤ ስለ አየር ንብረት ለውጥ ማሰብ ለጭንቀት እና ፍርሃት እንደዳረጋት ትናገራለች፡፡
 
የ24 አመቷ ፖርቹጋላዊት ነርስ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች የበርካቶች ህይወት እየተቀጠፈ በመሆኑ እያንዳንዷን ቀን በድባቴ ለማሳለፍ መገደዷንም ገልጻለች፡፡
 
በ6ቱ ወጣቶች እና በ32ቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መካከል የሚደረገው የህግ ሂደት “በዳዊት እና ጎሊያድ መካከል የነበረው ፍጥጫ አይነት ስሜት ቢኖረውም” ወጣቶቹን መደገፍ እንደሚገባ የግሎባል ሌጋል አክሽን ኔትዎርክ ዳይሬክተር ዶክተር ገሮይድ ኦኪዩን ተናግረዋል፡፡
 
ክሱ እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ ፍርድ ቤት እንደሚደመጥም ተነግሯል፡፡

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top