ለዩኒቨርስቲ ትምህርት 6 የምዕራብ አፍሪካ ሀገራትን በሳይክል አቋርጦ ግብጽ የገባው የ25 ዓመቱ ጊኒያዊ ለብዙዎች የአላማ ጽናት ተምሳሌት ሆኗል፡፡
ማማዱ ሳፋዮ ባሪ በጥንታዊው የግብጽ አል-አዝሀር ዩኒቨርስቲ ትምህርቱን ለመከታተል የነበረውን ህልም ለማሳካት ከሀገሩ ጊኒ በሳይክል ጉዞ የጀመረው ከ4 ወር በፊት ነበር፡፡
ተማሪው ማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ቶጎ፣ ቤኒን፣ ኒጀር እና ቻድን አቋርጦ ግብጽ የገባው 4 ሺህ ኪሎ ሜትሮችን በሳይክል ተጉዞ እንደሆነም ተነግሯል፡፡
ባለ ትዳር እና የአንድ ልጅ አባት የሆነው ማማዱ አለም ላይ ከፍተኛ ከበሬታ ባለው አል-አዝሀር ዩኒቨርስቲ ለመማር በሳይክል ባደረገው ጉዞ በቀጠናው ካለው የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ እና መፈንቅለ መንግስታት ካስከተሏቸው ቀውሶች ጋር ተጋፍጦ ማለፉንም ለቢቢሲ ገልጿል፡፡
ሁለት ጊዜ ቡርኪናፋሶ ውስጥ አንድ ጊዜ ደግሞ ቶጎ ውስጥ ታፍኖ መታሰሩንም ጠቁሟል፡፡
የመጨረሻውን የሳይክል ጉዞ ካደረገባት ቻድ ወደ ካይሮ መድረስ የቻለውም አንድ ጋዜጠኛ መንገድ ላይ አግኝቶት ጉዞውን ቀርጾ ማህራዊ የትስስር ገጾች ላይ ከለቀቀው በኃላ የአውሮፕላን ትኬት ወጪውን ለመሸፈን ፍቃደኛ የሆኑ መልካም ሰዎች በመገኘታቸው እንደሆነም አስታውቋል፡፡
የተማሪው ጽናት ያስደነቀው አል-አዝሀር ዩኒቨርስቲ ለማማዱ ሙሉ ስኮላርሺፕ መስጠቱን ይፋ አድርጓል፡፡