በኢትዮጵያ የእንግሊዝኛ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጁ ሰው፦ አቶ ያዕቆብ ወልደማሪያም

2 Mons Ago
በኢትዮጵያ የእንግሊዝኛ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጁ ሰው፦ አቶ ያዕቆብ ወልደማሪያም

በኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ ውስጥ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ በመሆን የሠሩት አቶ ያዕቆብ ወልደማሪያም ሹባ፣ ለኢትዮጵያ የእንግሊዘኛ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ዕድገት ከወጣትነት እስከ አረጋዊነት ዕድሜያቸው ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አስተዋጽኦ ያደረጉ አንጋፋ ጋዜጠኛ ናቸው።

በኢትዮጵያ የእንግሊዝኛ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ለ56 ዓመታት ሀገራቸውን እና ሕዝባቸውን ያገለገሉት አቶ ያዕቆብ፣ በአስደናቂ ስብዕናቸው እና በጠንካራ የሥራ ባህላቸው ይታወቃሉ።

አቶ ያዕቆብ ወልደማሪያም ሹባ በቀድሞው የወለጋ ጠቅላይ ግዛት ነቀምቴ ከተማ በ1921 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን፣ ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በሚኖሩበት ከተማ የጣሊያን ሚሲዮኖች ባቋቋሙት ትምህርት ቤት ተምረዋል። ከዚህ በመቀጠልም በኮተቤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በመከታተል ባስመዘገቡት የላቀ ውጤት ወደ እንግሊዝ ለመሄድ የሚያስችል ዕድል አግኝተዋል።

አቶ ያዕቆብ በእንግሊዝ በአንድ ታዋቂ ኮሌጅ ውስጥ በኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ተመድበው ትምህርታቸውን ቢጀምሩም፤ በጋዜጠኝንት እና ሥነ-ጽሑፍ ላይ የነበራቸው ፍላጎት እጅግ ከፍ ያለ እንደነበር በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል።

አቶ ያዕቆብ ለጋዜጠኝነት በነበራቸው ልዩ ፍቅር የተነሣ በእንግሊዝ ስኩል ኦፍ ለንደን ከሚማሩት የምሕንድስና ትምህርት ጎን ለጎን አልፎ አልፎ የጋዜጠኝነት ኮርስ ወስደዋል።

አቶ ያዕቆብ በለንደን እያሉ ጋዜጦችን በማንበብ ራሳቸውን በራሳቸው ያብቁ እንጂ፣ በመደበኛነት የጋዜጠኝነት ሙያን በዩኒቨርስቲዎች ወይም ኮሌጆች ውስጥ ገብተው አልተማሩም ነበር።

አቶ ያዕቆብ የጋዜጠኝነት ሕልማቸውን እውን ካደረጉበት የኢትዮጵያ ሄራልድ ከመግባታቸው በፊት በአምኃ ደስታ ትምህርት ቤት እና በነቀምቴ በሚገኝው የራስ መኮንን ትምህርት ቤት በመምህርነት ያገለገሉ ሲሆን፣ ለጥቂት ዓመታትም በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግለዋል።

በ1951 ዓ.ም በኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ተቀጥረው መሥራት የጀመሩ ሲሆን፣ በመጀመሪያ የቅጥር ዓመታቸውም ርዕሰ አንቀጽና መጣጥፎችን በልዩ ሁኔታ በማቅርብ እና በማዘጋጀት የጽሑፍ ችሎታቸውን አሳይተዋል። አቶ ያዕቆብ አንድ ዓመት እንደሠሩ በወቅቱ የኢትዮጵያን ሄራልድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበሩት ዶ/ር ዴቪድ ታልቦት ወደ ውጭ ሀገር በመሄዳቸው ምክንያት አቶ ያዕቆብ ዶ/ር ዴቪድን ተክተው በሄራልድ ጋዜጣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ ለመሆን ችለዋል።

በወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን በበላይነት የሚመሩት አቶ ዓምደ ሚካኤል ደሳለኝ የኢትዮጵያ ሄራልድ ጋዜጣ በኢትዮጵያዊ ዋና አዘጋጅ እንዲመራ ይመኙ ስለነበር አቶ ያዕቆብ በሄራልድ አቅማቸውን እንዲያወጡ ዕድል እንዳመቻቹላቸውም ይነገራል።

አቶ ያዕቆብ በሄራልድ በሠሩበት የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ጠንካራ አገራዊ ጉዳዮችን በማንሣት የሚታወቁ ሲሆን፣ ከእነዚህ ጉዳዮች መካከል ነዋሪዎች ገንዘብ ቆጥበው የቤት ባለቤት የሚሆኑበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ የሞገቱበት ጽሑፍ እና ሠራተኛው የጡረታ መብቱ ሊከበርለት ይገባል ሲሉ ያቀረቧቸው መጣጥፎች በእጅጉ ይታወቅላቸዋል።

አቶ ያዕቆብ የሄራልድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበሩበት ወቅት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ በሚገኙባቸው ሁነቶች ላይ በመገኘት የተለያዩ ዘገባዎችን በእንግሊዘኛ ቋንቋ በማዘጋጀት እና አዳዲስ የዘገባ አይነቶችን በማስተዋወቅ ጋዜጣው ይበልጥ እንዲጎለብት እና ተነባቢ እንዲሆን ትልቅ አስተዋፅኦ አድርገዋል።

ከሄራልድ ከለቀቁ በኋላ በመነን መጽሔት፣ በቮይስ ኦፍ ኢትዮጵያ፣ በአዲስ ሪፖርተር በኤዲተርነት የሠሩ ሲሆን፣ በሥራቸውም በብዙዎቹ የሙያ አጋሮቻቸው የተመሰከረላቸው ናቸው።

በቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ለ15 ዓመታት፣ በደርግ ዘመን ለ17 ዓመታት፤ ከዚያ በኋላ ላለፉት 24 ዓመታት በጠቅላላ ለ56 ዓመታት በሙያቸው ሀገራቸውንም አገልግለዋል።

አቶ ያዕቆብ ከ1983 በኋላ ዘሰን፤ ዘሪፖርተር፤ ፎከስ ለተሰኙ የኅትመት ውጤቶች ሠርተዋል። በእንግሊዝኛ ቋንቋ መጽሐፍትን ላሳተሙ ሰዎችም ሙያዊ ምክር በመስጠት ድጋፍ ማድረጋቸው ይነገራል።

ለኢትዮጵያ የእንግሊዝኛ ጋዜጦች እና መጽሔቶች ዕድገት ከወጣትነት እስከ አረጋዊነት የዕድሜያቸው እኩሌታ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉት አቶ ያዕቆብ፣ በጋዜጠኝነት እና ሚዲያ ዘርፍ ላበረከቱት ላቅ ያለ አስተዋጽኦ በ2007 የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት ተበረክቶላቸዋል።

ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም በሕይወት ሳሉ 10 ልጆች ሲያፈሩ፣ በሕይወት ካሉት 4 ወንድና 3 ሴቶች ልጆቻቸው ስምንት የልጅ ልጅ እንዲሁም አንድ የልጅ ልጅ ልጅ አይተዋል።

ጋዜጠኛ ያዕቆብ ወልደማርያም ባደረባቸው ህመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ94 ዓመታቸው ነሐሴ 15 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩ ሲሆን የቀብር ሥነ-ሥርዓታቸውም ቤተሰቦቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ነሐሴ 17 ቀን 2015 ዓ.ም በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top