ቻይና እና የአውሮፓ ሕብረትን ያፋጠጠው የኤሌክትሪክ መኪና

1 Yr Ago 1770
ቻይና እና የአውሮፓ ሕብረትን ያፋጠጠው የኤሌክትሪክ መኪና

የፈርስት ፖስት ተንታኝ የሆነችው ፓልኪ ሻርማ እንደምትገልጸው ቻይና ከአውሮፓ ጋር “የንግድ ጦርነት አፋፍ ላይ” ነች። እሷ እንደምትለው የዓለም ሁለተኛ የምጣኔ ሀብት ባለቤት የሆነችው ቻይና እና ሶስተኛ ደረጃን ከያዘው የአውሮፓ ሕብረት መካከል የሚደረገው የንግድ ጦርነት አደገኛ ነው።

የአውሮፓ ኮሚሽን ከመንግሥት በሚያገኙት ድጎማ የአውሮፓን ገበያ አዛብተዋል ያላቸውን ርካሽ የቻይና ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ አውሮፓ እንዳይገቡ ለመከላከል ምርመራ ጀምሯል።

የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ፎን ደር ሌየን ለሕብረቱ ፓርላማ ዓመታዊ ጉባኤ ባደረጉት ንግግራቸው “የዓለም ገበያዎች አሁን በርካሽ የኤሌክትሪክ መኪኖች እየተጥለቀለቁ ነው፤ ሰው ሰራሽ ርካሽነቱ የተፈጠረው በመንግሥት ከፍተኛ ድጎማ ነው” ብለዋል። ለዚህም ምርመራ እንዲጀመር ሀሳብ አቅርበዋል።

የአውሮፓ ባለስልጣናት የቻይና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ወደ ሕብረቱ ሀገራት መግባትን ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠር የሥራ ዕድል እና ወደ ውጭ በሚላኩት የአህጉሪቱ ተሽከርካሪዎች አደጋ ላይ ናቸው በሚል ፍርሃት ነው ምርመራ እንዲጀመር የተደረገው።

ኮሚሽኑ ከ9 እስከ 13 ባሉት ወራት ውስጥ በቻይና ላይ አሁን ካለው 10 በመቶ በላይ ታክስ ለመጣል ወይም ሌላ አማራጭ ሊጠቀም እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን ቀደም ሲል አሜሪካ በቻይና የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ላይ የጣለችው 27.5 በመቶ የሚጠጋ ታሪፍ ለመጣል ሀሳብ እንዳለውም ተነግሯል።

ሕብረቱ ከአስር ዓመት በፊት በቻይና የፀሐይ ፓነሎች ላይ ሊጥል የነበረውን እገዳ ከተወ በኋላ ከንግድ ጦርነት ማምለጥ ችሎ እንደነበረ ፊሊፕ ብሌንኪንሶፕ ለሮይተርስ ጽፏል። ብሌንኪንሶፕ “የአውሮፓ ሕብረት ይህንንስ ጦርነት ይጀምር ይሆን?” የሚል ጥያቄም አንስቷል ።

የፀረ-ድጎማ ምርመራው በቻይና እየተመረቱ ወደ አውሮፓ ገበያ የሚላኩ እንደ ቴስላ፣ ሬናውልት(Renault) እና ቢ.ኤም.ደብሊው (BMW) እንደሚያካትት የተገለጸ ሲሆን፣ የአውሮፓ ሕብረት የኢንዱስትሪዎቹን ችግር ከመፍታት ይልቅ የሌሎች ሀገሮችን ምርቶች ለማገድ እንቅስቃሴ መጀመሩ አነጋጋሪ ሆኗል።

የቻይና የንግድ ምክር ቤት በበኩሉ፣ የአውሮፓ ሕብረት ምርመራውን መጀመር በጣም ያሳሰበው እና የሚቃወመው መሆኑን ገልጾ፣ ይህ አካሄድ የዘርፉን ተወዳዳሪነት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ገልጿል። የቻይና መንግሥት ለዘርፉ ምንም ዓይነት ድጎማ እንደማያደርግ እና ሕብረቱ በቻይና የሚመረቱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በቅንነት እንዲመለከት ጠይቋል።

ቻይና 60 በመቶ የሚሆነውን የዓለም አቀፍ የኤሌክትሪክ መኪና ባትሪ ምርትን የምትሸፍን መሆኑ አውሮፓን አሳስቧል ነው የተባለው። የቻይና የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ ኢንዱስትሪዎች ገበያውን ከተቆጣጠሩ ከባድ ፈተና እንደሚገጥማቸውም ነው የተገለጸው።

እንደ ፋይናንሺያል ታይምስ ዘገባ እ.አ.አ በ2023 ብቻ በዓለም አቀፍ ደረጃ 560 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ከ14 ሚሊዮን በላይ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች እንደሚያድግ እና የአውሮፓ ሕብረት በፉክክሩ ከገበያ ተጠቃሚነት ሊወጣ እንደሚችል ስጋት ተፈጥሮበታል።

የፈረንሳይ ምጣኔ ሀብት ሚኒስትር ብሩኖ ለሜሬ በተወሰደው አቋም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፣ "ምርመራውን በደስታ እቀበላለሁ፤ ቻይና ለተሸከርካሪ ኢንዱስትሪዎቿ የምታደርገው ድጎማ የዓለም ንግድ ድርጅት ህግጋት ካላከበሩ አውሮፓ መዋጋት መቻል አለባት" ማለታቸውን ፖለቲኮ ዘግቧል።

ከሌሜሬ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የጀርመን ኢኮኖሚ ሚኒስትር ሮበርት ሃቤክም ውሳኔውን በደስታ መቀበላቸውን ጠቅሰው፣ "ይህ ፍትሃዊ ያልሆነ ውድድር ነው፤ ዝቅተኛ ዋጋ ያላቸውን መኪናዎች ከአውሮፓ ማውጣት አለብን፤ ትክክለኛ የገበያ ውድድር ውስጥ ለመቆየት ቀጥተኛ ወይም ቀጥተኛ ያልሆኑ ድጎማዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ አለብን" ብለዋል።

ነገር ግን ባለሥልጣናቱ ይህንን ቢሉም የአውሮፓ የመኪና ኢንዱስትሪዎች በተለይም የጀርመን አውቶሞቢል አምራቾች የኮሚሽኑ አካሄድ ትክክል እንዳልሆነ እየገለጹ ነው፤ አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ አውቶሞቲቭ ሎቢስት “ከቢዝነስ አንፃር አፀፋውን የመመለስ አደጋን ይፈጥራል” ብለዋል። ሻርማ በበኩሏ፣ ይህ የፀረ-ድጎማ ምርመራ ጥያቄ ከአውሮፓ መኪና ኢንዱስትሪዎች እና የኢንዱስትሪዎቹ ኃላፊዎች አልተነሳም፤ ይህ ሀሳብ የሕብረቱ ባለሥልጣናት ሀሳብ ነው።

በሕብረቱ እና ቻይና መካከል ያለው የንግድ ጦርነት ከኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ ባለፈም የቻይና ምርቶች የአውሮፓን ገበያ መቆጣጠራቸው ለሕብረቱ አሳሳቢ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል።

ቤልጂየማዊው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ኤኮ ኮየን ዴልውስ ለብራሰልስ ታይምስ በሰጡት ቃለ-መጠይቅ እንደገለጹት፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እና የኮቪድ 19 የፈጠሩት ጫና የዓለምን ገበያ እየፈተነው ነው፤ በዚህ ምክንያትም ሀገራት በራቸውን ለመዝጋት እየሞከሩ ነው ብለዋል። አክለውም፣ "አውሮፓ ከቻይና ጋር ካለው የንግድ ጦርነት አታመልጥም፤ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ወረርሽኙ እና በዩክሬን ያለው ጦርነት መጠናከር ትልቅ ስጋት ሆኗል" ብለዋል።

ይህ ሁኔታም የአውሮፓ ሕብረት በቻይና ምርቶች ላይ እቀባ እንዲያደርግ እንዳነሳሳው ዴልውስ ገልጸዋል። ይህም ሕብረቱ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በብዛት በማምረት ለአውሮፓ የምታቀርበው ቻይና የወሰደችውን ብልጫ ለመቋቋም መፍትሔ እንዲፈልግ አነሳስቶታል ይላሉ።

የምጣኔ ሀብት ዘጋቢዋ ቫለንቲና ሮሜ ፋይናንሺያል ታይምስ ላይ እንደጻፈችው፣ አውሮፓ በአሜሪካ የተተውን የገበያ ክፍተቷን ከሞላችላት ቻይና ጥገኝነት ለመውጣት አዳጋች እንደሚሆንባት ገልጻለች።

የአውሮፓ ሕብረት እ.አ.አ በ2019 ቻይናን “ስልታዊ ተቀናቃኝ” የሚል ስያሜ በመስጠቱ በሁለቱ የኢኮኖሚ ልዕለ ኃያላን መካከል ያለው የንግድ ውጥረት ጨምሯል፤ ይሁን እንጂ የዩሮስታት መረጃ እንደሚያሳየው ከቻይና ወደ አውሮፓ የሚመጡ ሸቀጦች ዋጋ በ2018 እና 2022 መካከል በእጥፍ ጨምሯል።

የፈርስት ፖስት ተንታኟ ፓልኪ ሻርማ በማጠቃለያ ላይ እንደገለጸችው፣ የአውሮፓ ሕብረት በቻይና የኤሌክትሪክ መኪናዎች ላይ ታሪፍ ለመጣል ያቀረቧቸው የሥራ ዕድል እና የገበያ ምክንያት ሽፋን ነው። ዋና ዓላማው ፖለቲካዊ እንደሆነ በማስታወስ ሁለት ምክንያቶችን ጠቅሳለች፤ የመጀመሪያው ቻይና የሩሲያ ወዳጅ ስለሆነች እንደ ስጋት በመታየቷ ሲሆን ሁለተኛው እና ዋነኛው ግን ከአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ቀጣይ ገበያውን የሚቆጣጠረው የኤሌክትሪክ መኪና ኢንዱስትሪ ላይ ቻይና ከአሁኑ የበለይነት እየያዘች መምጣቷ አሳሳቢ ስለሆነባቸው ነው ብላለች።

በለሚ ታደሰ


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top