ለብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ''ከዕዳ ወደ ምንዳ'' በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀው የመጀመሪያ ዙር ስልጠና በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በስልጠናው ከፌዴራልና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ሲሆን "ሀብት መፍጠር እና ማስተዳደር" በሚል መሪ ሀሳብ በአዳማ ከተማ የሚገኙ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝታቸው ኢትዮጵያን የሚያሻግሩ በርካታ የልማት ክንውኖች መኖራቸውን እንደተመለከቱ ገልጸው፤ የሀገሪቱን እድገትና ብልጽግና ለማረጋገጥ አመራሩን ጨምሮ የሕዝቡ ትብብርና የጋራ ልማት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያን እምቅ ሃብቶች በማልማትና በተገቢው መንገድ በማስተዳደር እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው አመራሮች የገለጹት።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍፁም አሰፋ፤ በሁሉም መስክ ያሉ የኢትዮጵያ እምቅ ሃብቶችን በአግባቡ ተረድቶ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ብልጽግና ፓርቲ በኢትዮጵያ በየትኛውም ጊዜ ባልታየ መልኩ የነበሩ ተግዳሮቶችን የሚያሻግሩ ስራዎች መስራቱን አንስተዋል።
በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የተከናወኑ ስራዎች ውጤት ማምጣታቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም ሁሉም አመራር ይህንን ታሳቢ ያደረገ ስራ ማከናወን እንዳለበት ጠቁመዋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፤ ያሉንን አቅሞች በሚገባ ስራ ላይ በማዋል ብልጽግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸው፤ የብዙ አገራት ስኬታማ ታሪክ የሚያሳየው ይህንኑ ነው ብለዋል።
የገቢዎች ሚኒስትሯ አይናለም ንጉሴም፤ ኢትዮጵያን መቀየር በአመራሩና በሕዝቡ እጅ ላይ ያለ ጉዳይ መሆኑንና ኢትዮጵያ ያሏትን ሁለንተናዊ ጸጋዎች ወደ ተጨማሪ አቅም ለመቀየር በጋራ መስራት ይገባል ብለዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ፤ ኢትዮጵያ በርካታ ሀብቶች ያሏት አገር መሆኗን ገልጸው፤ እነዚህን ሀብቶች ወደ ኢኮኖሚ ተጠቃሚነት መቀየር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከአስተሳሰብ እንዲሁም ከጊዜ አጠቃቀም አንጻር አመራሩ ለአንድ አላማ ቆርጦ መነሳት እንዳለበት ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ፤ ለድንገተኛ አደጋ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በተለይም 'ባንዴጅ' እና 'ጎውዝ' ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ምርት መተካታቸውን ገልጸዋል።
ይህም ከተደራሽነት እንዲሁም የውጭ ምንዛሪን ከማስቀረት አንጻር ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ገልጸው ለቀጣይ ስራዎች ትልቅ ግብአት የሚሆኑ ነገሮችን መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ደኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ፤ ያሉንን ሀብቶች መረዳት እና ማስተዳደር ከቻልን የወደፊቷን ኢትዮጵያ ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚቻል አመላክተዋል።
የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ፤ ኢትዮጵያ ያላትን ሃብት በአግባቡ መጠቀም ከቻልን በአጭር ጊዜ ወደ ጥሪት ማፍራት መሸጋገር እንደሚቻልም ነው ያስረዱት።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ያስሚን ወሀብረቢ፤ ኢትዮጵያ የሰው ሀይልን ጨምሮ የማዕድን እና የታዳሽ ሀይል ሀብት ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል።
እነዚህን ሀብቶች በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም ሀብትን በመፍጠር አገርን ወደ ተሻለ ብልጽግና ማምጣት እንደሚቻልም ነው ያመለከቱት።
እንደ ሚኒስትሮቹ ገለጻ የኢትዮጵያን እምቅ ሃብቶች በማልማትና በተገቢው መንገድ በማስተዳደር የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት አመራሩን ጨምሮ የህዝቡ ትብብርና የጋራ ጥረት ወሳኝ ነው ሲሉ መጠቆማቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።