የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ውሳኔ ማስተላለፉን በማስመልከት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ውሳኔ ማሳለፉን መሰረት አድርገው ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት፣ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ቀልብን ከሚስቡ የቱሪዝም ኃብቶቻችን መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
የጌዴኦ ህዘብ ደን የሰው ልጅ ህይወት መሆኑን ቀድሞ የተረዳና እንደልጁ ተንከባክቦ ከትውልድ ትውልድ የሚያሸጋግር አኩሪ ባህል ያለው ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ባህላዊ መልክዓ ምድሩም የዚህ ድንቅ ባህል ውጤት ነው በማለትም አብራርተዋል።
የክልሉ መንግስት የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ የዛሬው ውጤት እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፌደራል መንግስት ተቋማት ምስጋና ማቅረባቸውን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መረጃ ያመለክታል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በመግለጫቸው፣ የክልሉ መንግስት ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ለቅርሱ ዘላቂ እንክብካቤ በማድረግ፣ የቱሪዝም መስህብ እንዲሆን አበክሮ ይሰራልም ብለዋል።