ሪማቶይድ (rheumatoid arthritis) /የአንጓ ብግነት/ የሚከሰተው የሰውነታችን በሽታ መከላከያ ሕዋሶች በስህተት በራሳቸው ላይ በሚያደርሱት ጉዳት የሚፈጠር እና በመላው አካል የሚሰራጭ የብግነት /የማቃጠል/ በሽታ ነው፤ መገለጫውም በአንድ ጎን የሚከሰት የእጅ እና የእግር አንጓ ብግነት /የማቃጠል/ ስሜት ነው።
ሪማቶይድ ቀስ በቀስም አንጓዎችን ከጥቅም ውጪ የሚያደርግ በሽታ ነው። በዋነኝነት መገጣጠሚያዎችን የሚያጠቃ ሲሆን፣ ብዙውን ጊዜ በርካታ መገጣጠሚያዎችን በአንድ ጊዜ በማጥቃት ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።
ይህ የሕብረ ሕዋሳት ጉዳት ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ወይም ሥር የሰደደ ሕመም፣ ሚዛን መጠበቅ አለመቻል እና የአካል ጉዳተኝነት (የተዛባ ቅርጽ) ሊያስከትል ይችላል።
ከመገጣጠሚያ በተጨማሪ ሌሎች የሰውነታችን ሥሮችን በማጥቃት ሳንባ፣ ልብ፣ ዓይን፣ ቆዳ እና የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችንን ለችግር ይዳርጋል።
ሪማቶይድ በአብዛኛው ሴቶችን የሚያጠቃ ሲሆን በየትኛውም የዕድሜ ክልል የሚፈጠር ነው፤ ነገር ግን ከዕድሜ መግፋት ጋር ተያይዞ በበሽታው የመያዝ ዕድሉ ይጨምራል።
አንዳንድ ሰዎች በሪማቶይድ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፤ እነዚህ ሰዎች “HLA (Human leukocyte antigen) ክፍል II genotypes” የሚባሉ የዘረመል ዓይነት ያላቸው መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ። ዘረመሎቹ የበሽታውን ሁኔታ ያባብሳሉ።
እነዚህ ዘረመሎች ያላቸው ሰዎች አጫሽ እና ከመጠን በላይ ወፍራም ከሆኑ ለሪማቶይድ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ይሆናል።
ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሲጋራ የሚያጨስ ሰው በሪማቶይድ (በአንጓ ብግነት) የመያዝ ዕድል ይጨምራል፤ መጀመሪያውኑ በበሽታው የተያዘ ከሆነም በሽታው ሊባባስበት ይችላል።
ጨርሶ ያልወለዱ ሴቶች ለሪማቶይድ የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችልም የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የሪማቶይድ /የአንጓ ብግነት/ ምልክቶች
ከአምስት በላይ በአንድ ጎን ያሉ አንጓዎች ሕመም፣ የአንጓ እብጠት፣ ጠዋት ሲነሡ ሰውነትን ማጠፍ አለመቻል፣ የመገጣጠሚያ እንቅስቃሴ መቀነስ፣ የድካም ስሜት፣ አጠቃላይ የጡንቻ ሕመም እና የክብደት መቀነስ የበሽታው ምልክቶች ናቸው።
በሽታው ከመገጣጠሚያ ውጪ ሲከሰት ደግሞ፦ ሳል፣ የትንፋሽ ማጠር፣ የደረት ሕመም፣ የዓይን ዕንባ መድረቅ፣ የዓይን ሕመም እና መቅላት፣ ቆዳ ላይ እብጠት፣ መጥቆር እና መቅላት ምልክቶች ይታያሉ።
የእግርና እጅ መደንዘዝም የሪማቶይድ ምልክት ሲሆን - በዚህም እብጠት፣ እጅ ወይም እግር ሲነካ ምንም አለመሰማት የመገጣጠሚያ ጉዳት ይስተዋላል።
የሪማቶይድ ሕክምና
ለሕመም ማስታገሻ ተብሎ የሪማቶይድ መድኃኒቶች (methotrexate, chloroquine phosphate, steroid) ጥቅም ላይ ይውላሉ። ነገር ግን እነዚህን መድኃኒቶች ያለሐኪም ትዕዛዝ መወሰድ ፈፅሞ አይመከርም፤ ምክንያቱም የጎንዮሽ ጉዳታቸው የከፋ በመሆኑ። ይልቁንም በየጊዜው የሐኪም ክትትል ማድረረግ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎች ይመክራሉ።
በመገጣጠሚያዎችዎ ላይ የማያቋርጥ ምቾት መንሣት እና እና እብጠት ካለብዎ በአፋጣኝ ወደ ሐኪም ቤት ሊሄዱ ይገባል።
ሪማቶይድ (አንጓ ብግነት) ያለበት ሰው መመገብ የሌለበት ምግቦች
ሪማቶይድ ያለበት ሰው አልኮል መጠጣት የለበትም፤ ቀይ ስጋ፣ ቅባት የበዛበት ምግብ፣ ለስላሳ መጠጦች፤ የእንስሳት ተዋጽኦ (ወተት፣ እርጎ፣ አይብ)፣ ጨው የበዛበት ምግብ፣ ስንዴ፣ አብዝቶ መውሰድ የለበትም፤ በፋብሪካ የተቀናበረ ምግብም በብዛት ከመመገብ መቆጠብ ይጠበቅበታል ሲሉ የጤና ባለሙያዎች ምክራቸውን ይለግሳሉ።