በሞሮኮ ታሪክ አስከፊ የተባለው የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ተከሰተ?

10 Mons Ago
በሞሮኮ ታሪክ አስከፊ የተባለው የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ተከሰተ?

ባለፈው ሳምንት በሞሮኮ የደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ እጅግ አስከፊ እና የዓለምን ህዝብም በእጅጉ ያሳዘነ ክስተት ነበር። አደጋው ከደረሰበት ቀን ጀምሮ የነፍስ አድን ሰራተኞች የፈራረሱትን ድንጋዮች በፈነቀሉ ቁጥር የሟቾች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

የሀገሪቱ አራተኛ ትልቋ ከተማ ከሆነችው ማራኬሽ 75 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዋ እና ወደ 840 ሺህ ሰዎች በሚኖሩባት አትላስ ሰንሰለታማ ተራራ ላይ የተቀሰቀሰው የመሬት መንቀጥቀጥ በስተሰሜን እስከምትገኘው ካዛብላንካ ድረስ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ነበር። አደጋው በአትላስ ተራሮች አቅራቢያ ያሉትን ከተሞች እና መንደሮች በከፍተኛ ሁኔታ ጎድቷል፣ የማራኬሽ ከተማ መንደሮችንም አውድሟል።

የመሬት መንቀጥቀጡ በሬክተር ስኬል በሚለካበት ጊዜ 6.8 ያህል መጠን ያስመዘገበ ሲሆን፤ ይህም በሞሮኮ ታሪክ ከፍተኛ እና አደገኛ አስብሎታል።

ለመሆኑ በሞሮኮ ታሪክ አደገኛ የተባለው ይህ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዴት ሊከሰት ቻለ?

የመሬት መንቀጥቀጥ በምድር ንጣፍ ወይም ቴክቶኒክ ፕሌት በሚሰኘው የመሬት ክፍል ላይ የሚፈጠር ክስተት መሆኑን የዘርፉ ተመራመሪዎች ይገልፃሉ። መሬት ከተለያዩ ንብርብሮች (layers) የተፈጠረ አካል ሲሆን፤ እነዚህም ክረስት፣ ማንትል እና ኮር በሚል በሦስት ዋና ክፍሎች የተከፈለ ነው።

ቴክቶኒክ ፕሌትች ምድራችን ከታነፀችባቸው ንብርብሮች የላይኛውን ክፍል ይዘው በመሀለኛው ክፍል ማንትል ላይ በመንተራስ የሚንቀሳቀሱ እና የምድራችን የላይኛውን ክፍልንም ከፋፍለው የሚገኙ የመሬት አካላት ናቸው።

የመሬት መንቀጥቀጥ የሚፈጠረው ከምድር በታች በሚገኙ በእነዚህ አለታማ ቁሶች ግጭት ሲሆን፤ ይህ ግጭት የሚፈጠረው የምድር ንጣፎች ወይም "ቴክቶኒክ ፕሌትስ" በሚሰኙት ጠርዝ ላይ መሆኑን ተመራማሪዎች ይገልፃሉ።

እነዚህ የምድር ቅርፊቶች የተደራረቡ እና ሁልጊዜ በእንቅስቃሴ ላይ ያሉ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግን እርስ በእርስ የሚተሻሹበት እና የሚጋጩበት ጊዜ አለ። ይህ ድንተኛ ግጭት የሚፈጥረው ንዝረት እና ሞገድ ደግም ምድርን በመሰንጠቅ የመሬት መንቀጥቀጥ እንዲፈጠር ያደርጋል።

በምድር የላይኛው ክፍል ዘጠኝ ትላልቅ ቴክቶኒክ ፕሌቶች እንዳሉ የሚነገር ሲሆን፤ እነዚህም ሰሜን አሜሪካ፣ ፓስፊክ፣ ዩሮኤዥያ፣ አፍሪካ፣ አውስትራሊያ፣ ህንድ፣ ደቡብ አሜሪካ፣ ህንድ-አውስትራሊያ እና አንታርክቲክ የሚል ስያሜ ተሰጥቷቸዋል።

እነዚህ ቴክቶኒክ ፕሌቶችም ከስራቸው ባለው ማንትል በመባል በሚታወቀው የቀለጠ አለት የተነሣ በዓመት ከ1.5 እስከ 2 ሴንቲሜትር ያህል እንደሚንቃሰቀሱ የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ። ቴክቶኒክ ፕሌቶች የሚገናኙበት ቦታ ለመሬት መንቀጥቀጥ፣ ለእሳተ ገሞራ መቀስቀስ እና ለከፍተኛ ማዕበል የተጋለጠም ነው።

እነዚህ ቴክቶኒክ ፕሌቶች ጎን ለጎን በመንሸራተት፣ እርስ በእርስ በመደራረብ እና ከላይ ወደታች በመንሸራተት ሲንቀሳቀሱ ምንም አይነት ድምፅ ባይኖራቸውም፤ አንዳንዴ ግን እንቅስቃሴያቸው ከዝግታ ሲያልፍ የሚያሰሙት ድምፅ በመጠኑም ቢሆን ለሰዎች ይሰማል።

ሁለት የተለያዩ ቴክቶኒክ ፕሌቶች በሚንቀሳቀሱበትም ጊዜ የሚገጣጠሙበት ቦታ ላይ በሚፈጠረው ከፍተኛ ግጭት እና ከፍተኛ ንዝረት የተነሣ የመሬት መንቀጥቀጡ ይከሰታል። በዓለማችን ላይ የምናያቸው ተራራዎች፣ ሸለቆዎች እና አዳዲስ የመሬት መዋቅሮች በእነዚህ ቴክቶኒክ ፕሌቶች የተነሣ የሚፈጠሩ መሆናቸውንም ተመራማሪዎች ያስረዳሉ።

በዚህ ተመራማሪዎች ትንትና መሰረት በአፍሪካ ፕሌት ውስጥ በምትገኘው ሞሮኮ የተቀሰቀሰው የሰሞኑ አስከፊ የመሬት መንቀጥቀጥ የአፍሪካ እና የዩሮኤዥያ ቴክቶኒክ ፕሌቶች ሲንቀሳቀሱ የፈጠሩት ሲሆን፤ ንቅናቄው ከማራኬሽ ከተማ አንሥቶ በስተሰሜን እስከምትገኘው ካዛብላንካ ድረስ መሰማቱ ተገልጿል።

የአፍሪካ እና የዩሮኤዥያ ፕሌቶች ሲንቀሳቀሱ በመካከላቸው በሚፈጠር ከመሬት በታች በነበረ ግፊት እና ንዝረት ምክንያት አንደኛው የድንጋይ ጠርዝ በሌላው የዓለት ጠርዝ ስር በሚንሸራተት ጊዜ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል ሲለካ 6.8 መጠን እንደነበረው ተዘግቧል።

የመሬት መንቀጥቀጥ አስከፊነቱ የሚለካው በሚፈጥረው የግፊት መጠን ሲሆን፤ ዝቅተኛው 1 ከፍተኛው ደግሞ 10 ሬክተር ስኬል መሆኑን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

ሞሮኮ ያጋጠማት የመሬት መንቀጥቀጥ በሬክተር ስኬል 6.8 ሲሆን ይህም በሀገሪቱ ታሪክ አስከፊ የሚባል ነው።

ሞሮኮ የዚህን ዓይነት ከባድ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ከገጠማት ከ60 ዓመታት በላይ አስቆጥራለች። የሟቾች ቁጥር ወደ 3 ሺህ በተጠጋበት በዚህ ተፈጥሯዊ አደጋ፤ የቆሰሉ እንዲሁም የጠፉ ሰዎችም ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መጥቷል።

ለመሬት መንቀጥቀጥ አዲስ ያልሆነችው ሞሮኮ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተለያየ መጠን ባላቸው የመሬት መንቀጥቀጦች ተመታለች። ከዚህ በፊት ከፍተኛ መጠን ተብሎ የተመዘገበው ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 6 ሲሆን፤ ይህም ከአሁኑ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ መጠን ያለው ነው።

ባለፈው ሳምንት ዓርብ ምሽት በሞሮኮ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ባለፉት 25 ዓመታት ብቻ በዓለማችን ላይ ከተመዘገቡ እጅግ በጣም ከባድ እና ገዳይ የሆነ የመሬት መንቀጥቀጥ ከተከሰተባቸው ሀገራት ተራ እንድትመደብ አድርጓታል።

6.8 ሬክተር ስኬል መጠን የነበረው የመሬት መንቀጥቀጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ፣ ያቆሰለ እና ብዙዎችንም ያፈናቀለ ነው።

በዚሀ በያዝነው ዓመትም እንዲሁ በቱርክ እና ሶሪያ በተከሰተ 7.6 መጠን ባለው የመሬት መንቀጥቀጥ ከ21ሺ 600 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል።

ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ በቻይና ብቻ 87,500 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ የመሬት መንቀጥቀጥ የተከሰተ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ጃፓን፣ ኢራን፣ ኔፓል፣ ፊሊፒንስ እና ፔሩ በተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ የሚከሰትባቸው ሀገራት ሆነው ተመዝግበዋል።

ሞሮኮም እንዲሁ የመሬት መንቀጥቀጥ በብዛት የሚያጠቃት ሀገር ስትሆን፤ እ.ኤ.አ በ1960 በጋዲር ከተማ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ 15ሺህ የሚሆኑ ዜጎቿን ህይወት ነጥቆባታል። 5.8 መጠን የነበረው የመሬት መንቀጥቀጥ አጋዲር ከተማን ከመታ ወዲህ የዘንድሮው በታሪክ ከተመዘገበው እጅግ የከፋው የመሬት መንቀጥቀጥ ነው ተብሏል።

በሞሮኮ ደቡባዊ የአትላንቲክ የባህር ዳርቻ የምተገኘው አጋዲር ከተማ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት የፈራረሰች ሲሆን፤ አንድ ሶስተኛ የሚሆነው ህዝቧ አልቋል፣ ንብረት ወድሟል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፍርስራሽ ስር ተቀብረዋል።

እ.ኤ.አ. የካቲት 2004 በሰሜን ሞሮኮ እንዲሁ በደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ ወደ 630 የሚጠጉ ሰዎች ሲሞቱ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል ወደ 15,000 የሚጠጉት ቤት አልባ ሆነዋል።

ባለፈው ሳምንት በሞሮኮ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ በማራኬሽ እና አካባቢው ከ300,000 በላይ ሰዎች መጉዳቱን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበችው ማራኬሽ መዲና በመሬት መንቀጥቀጡ እንዳልነበር ሆናለች። ታሪካዊ ቦታዎች ወድመዋል፣ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ በርካታ አሮጌ ሕንፃዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ አንዳንዶቹ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ፈርሰዋል።

በአደጋው የተጎዱ የተወሰኑ አካባቢ ነዋሪዎች የምግብ እና የውሃ አቅርቦት ቢደረግላቸውም፤ በግዙፍ ድንጋዮች የተዘጉት መንገዶች ለአደጋ ሰራተኞት በቀላሉ ወደ ስፍራው ለመድረስ እንዳይችሉ በማድረጋቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ አሁንም እርዳታ ማድረስ አለመቻሉ ተገልጿል።

ሞሮኮ በአደጋው የተጎዱ አካባቢዎችን ለመርዳት አምቡላንሶችን፣ የነፍስ አድን ሠራተኞችን እና ወታደሮችን ወደ ክልሉ አሰማርታለች። የእርዳታ አቅራቢ ቡድኖች የሃገሪቱ መንግስት ሰፊ የእርዳታ ጥሪ እንዳላቀረበ እና የተወሰነ የውጪ እርዳታ እንደተቀበለ ገልፀዋል።

የሃገሪቱ መንግስት የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ያቀረቡትን የእርዳታ ጥሪ ችላ በማለት የዓለም አቀፍ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ከስፔን፣ ኳታር፣ ብሪታንያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ እርዳታ እየተቀበለ መሆኑን የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

የሞሮኮ መንግስት የሶስት ቀናት ብሄራዊ ሀዘን ባወጀበት በዚህ ተፈጥሮኣዊ አደጋ፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት አልባ ሲሆኑ፤ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ሆነዋል። የነፍስ አድን ሰራተኞች በፍርስራሹ ስር ተቀብረው የሚገኙ ሰዎችን ለመታደግ አሁንም ጥረት እያደረጉ ይገኛል። 

በሶስና ምንዳ 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top