የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶኻን ይህን ሀሳብ ያቀረቡት ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሶቺ ተገናኝተው በተወያዩበት ወቅት ሲሆን፣ በሁለትዮሽ የንግድ ልውውጥ ብሔራዊ ገንዘቦችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።
ፕሬዚዳንቱ "የማዕከላዊ ባንኮቻችን ኃላፊዎች ዛሬ እዚህ መገናኘታቸው ግብይታችንን ወደ ብሔራዊ ገንዘቦቻችን ለማሸጋገር ከሚደረገው እርምጃ አንጻር አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ" ብለዋል፡፡
አርዶኻን አክለውም "በአሁኑ ጊዜ የሁለትዮሽ ንግድ ልውውጡ 62 ቢሊዮን ዶላር መድረሱ እና ግባችን ወደ ሆነው 100 ቢሊዮን ዶላር እየተጓዝን በመሆኑም በጣም ደስ ብሎኛል" ብለዋል።
ፕሬዚዳንት ፑቲን በበኩላቸው በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ እድገት ፍጥነት አዎንታዊ ሆኖ እንደሚቀጥል እና ኢኮኖሚያዊ ትብብሩ እንደ ግብርና እና ኢነርጂ ባሉ ዘርፎች እየሰፋ እንደሚሄድ ጠቁመዋል።
ሁለቱ ሀገራት የጂኦፖለቲካዊ ልዩነት ቢኖራቸውም የኢኮኖሚ ትስስራቸውን ለማጠናከር እየሰሩ ሲሆን፣ ፑቲን እና ኤርዶኻን ባለፈው ሚያዚያ ወር የጋራ ኢንቨስትመንቶችን ለማበረታታት እና የንግድ ለውውጡን ለማሳደግ መስማማታቸውን አር.ቲ ዘግቧል፡፡