የጉበት መመረዝ ምንድነው?

1 Yr Ago 2824
የጉበት መመረዝ ምንድነው?

የጉበት መመረዝ መርዛማ ነገሮች በጉበት ውስጥ በሚጠራቀሙበት ጊዜ የሚከሰት ሲሆን፤ በርካታ ምክንያቶች የጉበት መመረዝን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ዋነኛው የጉበት ጥቅም መርዛማ ነገሮችን ከሰውነታችን ጠራርጎ ማስወጣት ወይም ማስወገድ ነው። ለእነዚህ መርዛማ ነገሮች ለረጅም ጊዜ በምንጋለጥበት ወቅት ከፍተኛ የጉበት ጉዳቶችን  ያመጣሉ። በዚህ አማካኝነትም  የጉበት መመረዝ ሊከሰት ይችላል

ጉበት ላይ  ጉዳት ከሚያደርሱ ምክንያቶች መካከል መድሃኒቶች ተጠቃሽ  ናቸው። መድሃኒት በምንወስድበት ጊዜ ጉበታችን በመድሃኒቱ ውስጥ ያሉ ንጥረ ነገሮችን ይሰባብራቸዋል። ከዚያም በሀሞት እና ሽንት አማካይነት ከሰውነታችን ውጪ ያስወግዳቸዋል፤ በመጨረሻም ተረፈ ምርቶች ይመረታሉ።

እነዚህ ተረፈ ምርቶች በጉበት ውስጥ ይቆያሉ፤ መድሃኒቶቹ ኬሚካል ስለሆኑ ለጉበት መርዛማ ይሆናሉ ከዚያም የጉበት ኢንፍላሜሽን ያስከትላሉ። በመጨረሻም ጉበት ስራውን ያቆማል ለህይወትም አስጊ ደረጃ ላይ ያደርሰናል።

 

ጉበትን የሚጎዱ ነገሮች:-

1.የአልኮል መጠጦች

አልኮል  ከፍተኛ  የጉበት መመረዝን የሚያስከትል ነው። አልኮል አብዝቶ መጠጣት ጉበት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል።ከብዙ ጊዜ ቆይታ በኃላ የጉበት ሄፓታይተስ ያስከትላል።በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ ጉበት ስራውን ያቆማል፤ ይህም ሁኔታ ደግሞ እስከሞት ድረስ የሚያደርስ ነው። 

  1. መድሃኒቶች የጉበት መመረዝን ያስከትሉ ይችላሉ

ኦጉመንቲን፣ ሀሎቲን፣ አይሶኒያዛይድ፣ ቫልፕሮክ አሲድ ፌናይታዮን፣ አዛታዮፕሪን፣

ኒያሲን፣ ሎቫስታቲን፣ ፕራቫስታቲን፣ ሲምቫስታቲን፣ ፍሉቫስታቲን፣ ሮሱቫስታቲን፣

ኬቶኰናዞል እና አንዳንድ የፀረ ባክቴሪያና ቫይረስ ያሉ መድሃኒቶች ለጉበት መመረዝ እንደምክንያትነት ይጠቀሳሉ።

ያለ ማዘዣለህመም ማስታገሻ የሚወሰዱ መድሃኒቶች ለረጂም ጊዜ ወይም በብዛት ሲወሰዱ  ድንገተኛ የሆነ ከፍተኛ መጠን ያለው መርዝ ጉበት ላይ እንዲፈጠር ያደርጋል።

ሌላው እነዚህን መድሃኒቶች እንደ አልኮል ካሉ ሌሎች መርዛማ ነገሮችጋር አብሮ መውሰድ ይህን ጉዳት በእጥፍ ይጨምረዋል። ዋነኛውና የመጀመሪያው የጉበት ስራ ማቆም

መነሻ ምክንያቶች መድሃኒቶች እንደሆኑ ይነገራል።

  1. ኬሚካሎች

በገበያ ላይ እና በተለያዩ ኢንደስትሪዎች የሚገኙ ኬሚካሎች የጉበት ጉዳት

ሊያመጡ ይችላሉ።

ካርበን ቴትራክሎራይድ (በደረቅ እጥበት የምንጠቀምባቸው)ቪናይል ክሎራይድ (የተለያዮ ፕላስቲኰችን ለመስራት የሚያገለግል)  የመሳሰሉ ኬሚካሎች በከፍተኛ ደረጃ ጉበት ላይ ጉዳት ያደርሳሉ

  1. ለመድሃኒትነት የሚጠቅሙ ተክሎችና የምግብነት ይዘት ያላቸው ተጨማሪ ምግቦች

በብዛት ስንወስዳቸው የጉበት ጉዳት የሚያመጡ በተፈጥሮ የሚገኙ

ለመድሃኒትነት የሚጠቅሙ ተክሎች አሉ። በተለይ በኢትዮጵያ ለህክምና የሚውሉ የባህል

መድሃኒቶች ምን ያህል መጠን መወሰድ እንዳለባቸው ስለማይታወቅ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ከነዚህ መድሃኒቶች መካከል የሚጠቀሱት፦ ካስካራ፣ ቻፓራል፣ ኮምፍሬይ፣ ካቫ፣ ኢፌድራ ይገኙበታል።

በተጨማሪም አንዳንድ ተጨማሪ ምግቦች በብዛት ሲወሰዱ የጉበት መመረዝን ያስከትላሉ። በተለያዮ አጋጣሚዎች ህፃናት እነዚህ ምግቦች ከረሜላ ስለሚመስላቸው ሊመገቸውና ለጉዳት ሊዳረጉ ይችላሉ፡፡

 

  የጉበት መመረዝ ምልክቶች:-

 1.የሆድ ህመም

ጉበታችን የሚገኘው በጎድን አጥንታችን አካባቢ ሲሆን የጉበታችን ጤናማ

አለመሆን በሆዳችን እና በጎድን አጥንታችን አካባቢ ከፍተኛ የህመም ስሜት ይፈጥራል፡፡

 2.የቆዳ ቀለም መቀየር/መለወጥ:-

በአይናችን ልናየው የምንችለው የጉበት ጉዳት/በሽታ ምልክት የቆዳ ቀለም ለውጥ ነው፡፡ የቆዳዎ ቀለም ቢጫ ወይም የገረጣ/የፈዘዘ እየሆነ ከመጣ ጉበትዎ በትክክል ስራውን እየተወጣ አይደለም ማለት ነው፡፡

  1. በተደጋጋሚ ማግሳት

በሆድ/አንጀት በአየር መነፋት ምክንያት በተደጋጋሚ በግሳት የሚሰቃዩ ከሆነ ጉበትዎ ምግብን ለመፍጨት የሚሆን ኢንዛይም ማምረት ተስኖታል ማለት ነው፡፡ በተጨማሪም የምግብ መፍጨት ስርዓት በጉበት ችግር ምክንያት ይታወካል፡፡

  1. የድካም ስሜት መሰማት

ጉበት ምግብን በሚሰባብርበት/እንዲፈጭ በሚያደርግበት ጊዜ በየቀኑ ስራችንን ለመስራት የሚጠቅም ሃይል/ጉልበት እንድናገኝ ያደርጋል፡፡ በቀላሉ የምንደክም ከሆነ የጉልበት ማጣት ምልክት ነው፤ ይህም ጉበታችን ሥራውን በትክክል አለመወጣቱን ያሳያል፡፡

  1. የሽንት ቀለም መለወጥ

ጉበታችን መጎዳት በሚጀምርበት ጊዜ የሽንታችን ቀለም ጠቆር ወዳለ ቢጫ ይቀየራል፤ አንደንዴም ወደ ደም ቀለም ሊወስደው ይችላል፡፡

በቂ ውሃ እወሰዱም ይህ የቀለም ለውጥ ከተከሰተ የጉበት ጤና ታውኳል ማለት ነው፡፡

  1. ቆዳን ማሳከክ

የጉበት በሽታ ማሳያ ከሆኑት አንዱ የቆዳ ማሳከክ ነው፡፡ በቆዳዎ ላይ

የሚያሳክክ ቦታ ካለ እና ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ ከመጣ የጉበት ችግር ሊሆን ይችላል፡፡

  1. ማቅለሽለሽ

የምግብ አለመፈጨት እና የአሲድ አለመመጣጠን የጉበት ጉዳት ምልክቶች ናቸው፡፡ የምግብ አለመፈጨት እና ማቅለሽለሽ የአመጋገብ ሁኔታችንን በመቀየር የማይስተካከል ከሆነ የጉበት ችግር ምልክት ነው፡፡ እየተባባሰ ሲሄድ ማስታወክ ደረጃ ላይ ይደርሳል።

  1. የክብደት መቀነስ

ድንገተኛ የሆነ የክብደት መቀነስ እንደ ጉበት ችግር ሊታይ ይችላል፡፡ ሳይፈልጉ ክብደት የሚቀንሱ ከሆነ የምግብ ፍላጎት መቀነስ ሊሆን ይችላል፤ ይህም የሚሆነው ጉበታችን ደካማ ስለሚሆን ሲሆን ቀጭን እና የተጎዳ ሰውነት እንዲኖረን ያደርገናል።

  1. ፈሳሽን መያዝ

በተላያዩ የሰውነት ክፍሎች ላይ ፈሳሾች መቋጠር/መያዝ በተለይ በእግር

አካባቢ ከታየ ይህ የታመመ ጉበት ምልክት ነው፡፡

ይህ ሁኔታ ኢዴማ ይባላል ፤ ይህ እብጠት በጉልበት፣ እጅ አና እግር ጣቶች አካባቢ ይከሰታል፡፡

ያበጡትን ጣቶች ስንጫናቸው ለጥቂት ሰከንዶች ወደ ውስጥ ገብተው/ጎድጉደው ይቀራሉ፡፡

  1. የአይነ ምድር ቀለም መቀየር

 የአይነ ምድር ቀለም መቀየር አንዱ የጉበት ችግር ምልክት ነው፡፡ ትንሽ ደም ከአይነ ምድር ጋር ተቀላቅሎ የሚወጣ ከሆነ ይህም ምልክቱ ነው፡፡ ሌላው ከአይነምድር ጋርየተያያዘ የጉበት ችግር ምልክት የሆድ ድርቀት ነው፡፡

እነዚህ  የጉበት መመረዝ ምልክቶች ከታየብዎ በአፋጣኝ  ወደ  ጤና ማዕከላት መሄድ ያስፈልገዎታል ፡፡

 

 ጉበት በሽታን  መከላከያ መንገዶች

  • የአልኮል መጠጥ እና ሲጋራ ማጨስ ማቆም

  • ማንኛውንም አይነት መድኃኒት ከመውሰዳችን በፊት ለጉበት ጉዳት የማያጋልጥ መሆኑን ማረጋገጥ

  • ያልተረጋገጡ የባህል መድኃኒቶችን ከመውሰድ መቆጠብ

  • በቂ እረፍት ማድረግ

  • ጫና የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ መቆጠብ

  • እንደ ሲርሆሲስ እና የጉበት ጮማ መኖራቸውን ለማረጋገጥ በየጊዜው ክትትል ማድረግ

  • ከታማሚው ጋር በጋራ የሚኖሩ ሰዎች ካሉ ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ መኖሩን ለማረጋገጥ የደም ምርመራ ማድረግ፤ እንዲሁም ክትባት መውሰድ
  • አመጋገባችን ማስተካከል፤ ጉበትን ለማጣራት እና ለማፅዳት የሚያግዙ ምግቦችን ለምሳሌ አቮካዶ፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ፖም ፣ ካሮት ፣ ባቄላ፣ ሙዝ እና የመሳሰሉትን አዘውትሮ መመገብ ዋና ዋናዎቹ ናቸዉ፡፡

በሜሮን ንብረት

 


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top