በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው የፅንፈኞች እንቅስቃሴ ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

3 Mons Ago
በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው የፅንፈኞች እንቅስቃሴ ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል - ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ያለው የፅንፈኞች እንቅስቃሴ ስጋት ወደ ማይሆንበት ደረጃ ላይ መድረሱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለፁ።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከመከላከያ ሚዲያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለሀገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ኃይሎች አሁን ላይ ስጋት ወደማይሆኑበት ደረጃ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

የመከላከያ ሰራዊቱ ጥበብ በታከለበት ወታደራዊ እንቅስቃሴ ተከስተው የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን እየቀረፈ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በአማራ ክልል የህዝቡን የመብት ጥያቄ ካባ በማድረግ ፍላጎቱን በኃይል ለማሳካት የተንቀሳቀሰው ኃይል ላይ እየተወሰደ ባለው እርምጃ አመርቂ ውጤት መመዝገቡንም ገልጸዋል።

የተከበረውን የፋኖ ስም መጠቀሚያ በማድረግ የክልሉን ፀጥታ ሲያውኩ የነበሩ ኃይሎችን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም ፋኖ ከጥንት ጀምሮ ሀገር ተወረረች ሲባል ጦርና ጋሻ ይዞ ለኢትዮጵያ ነፃነት የሚሰለፍ እንጂ መልሶ የሀገሩ ሰራዊት ላይ ጦር የሚመዝ አይደለም ብለዋል።

አሁን ላይ በፋኖ ስም እየተንቀሳቀሰ ያለው ኃይል በዘረፋ ተግባር ላይ የተሰማራና መንገዶችን በመዝጋት የህዝቡን ሰላም የሚያወክ ነው ማለታቸውም ተመላክቷል።

ህዝብን ሰላም ሲነሳ የነበረው ኃይልም የሰራው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ መልሶ እርቃኑን እንዲቀር እንዳደረገና አሁን ከህዝቡ እየተነጠለ ያለውን ይህን ኃይል አቅሙን በማዳከም ስጋት ከማይሆንበት ደረጃ ማድረስ ተችሏልም ሲሉ ገልፀዋል።

አገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ሆነው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ የሚነዙ ኃይሎች ለሀገርና ለህዝብ ሲል ውድ ህይወቱን እየከፈለ ሰላም የሚያረጋግጠውን ሰራዊት ስነ-ልቦና ያልተረዱ ናቸው ብለዋል።

ኢታማዦር ሹሙ አክለውም ሰራዊቱ በተሰማራባቸው የግዳጅ ቀጠናዎች ሁሉ ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮውን በአስተማማኝ እየተወጣ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የፅንፈኞች የሀሰት ፕሮፖጋንዳን የተገነዘበው ህዝባችን ከመከላከያ ሰራዊቱ ጎን በመሆን ለሰላሙ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።

በሀሰተኞች ሴራ ተታለው ከፅንፈኞች ጋር የተሰለፉ ወጣቶች በሰላማዊ መንገድ ወደ ህዝቡ እንዲመለሱም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጥሪ አስተላልፈዋል።

መከላከያ በ2015 በጀት ዓመት ተልዕኮውን በሚገባ መፈፀሙን የገለፁት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በ2016 በጀት አመትም እንደ ተቋም የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ከምን ጊዜውም በላይ ዝግጁ ነው ብለዋል።


አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ግብረመልስ
Top